የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 32

32
የወርቅ ጥጃ
1ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ ብዙ እንደ ቈየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፣ “ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት#32፥1 በዚህ እንዲሁም በቍጥር 23 እና 31 ላይ አምላክ ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም” አሉት።
2አሮንም፣ “የሚስቶቻችሁን፣ የወንድና የሴት ልጆቻችሁን የጆሮ ወርቅ አውልቃችሁ ወደ እኔ አምጡ” ብሎ መለሰላቸው። 3ሕዝቡም ሁሉ የጆሮ ወርቃቸውን አውልቀው ወደ አሮን አመጡ። 4እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ያወጡህ አማልክት#32፥4 በዚህና በቍጥር 8 ላይ፣ ይህ አምላካችሁ ነው። እነዚህ ናቸው” አሉ።
5አሮን ይህን ባየ ጊዜ በወርቅ ጥጃው ፊት ለፊት መሠዊያ ሠርቶ፣ “ነገ ለእግዚአብሔር በዓል ይሆናል” ብሎ ዐወጀ። 6በማግስቱም ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት#32፥6 በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል። አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ።
7ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ከግብጽ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ” አለው። 8“ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ አሉ።”
9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ ዐንገተ ደንዳናዎችም ናቸው። 10አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
11ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብጽ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነድዳል? 12ግብጻውያን፣ ‘በተራሮቹ ላይ ሊገድላቸው፣ ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ። 13ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።” 14ከዚያም እግዚአብሔር ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።
15ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላት በእጆቹ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቱም ከፊትና ከኋላ በሁለቱም ጐኖች ተጽፎባቸው ነበር። 16ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ በጽላቱ ላይ የተቀረጸ ጽሕፈትም የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበር።
17ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፣ “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ አለ አለው።”
18ሙሴም፣
“የድል ድምፅ አይደለም፤
የሽንፈትም ድምፅ አይደለም፤
የምሰማው የዘፈን ድምፅ ነው”
ብሎ መለሰለት።
19ሙሴ ወደ ሰፈሩ ደርሶ ጥጃውንና ጭፈራውን ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ፤ ጽላቱን ከእጁ በመወርወር ከተራራው ግርጌ ሰባበራቸው። 20ያበጁትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ከዚያም ዱቄት እስኪሆን ፈጨው፤ በውሃ ላይ በተነው፤ እስራኤላውያንም እንዲጠጡት አደረገ።
21ሙሴም አሮንን፣ “ወደዚህ አስከፊ ኀጢአት ትመራቸው ዘንድ እነዚህ ሕዝብ ምን አደረጉህ?” አለው።
22አሮንም መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አትቈጣ” ብሎ መለሰለት፤ “ይህ ሕዝብ ሁልጊዜ ለክፋት ያዘነበለ መሆኑን አንተ ታውቃለህ። 23እነርሱም ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም’ አሉኝ። 24ስለዚህ፣ ‘ማንኛውም ዐይነት የወርቅ ጌጣጌጥ ያለው ሁሉ ያውልቀው’ አልኋቸው፤ ከዚያም ወርቁን ሰጡኝ፤ ወደ እሳቱ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።”
25ሕዝቡ ከቍጥጥር ውጭ እንደ ሆኑ፣ አሮንም መረን እንደ ለቀቃቸውና በጠላቶቻቸውም ዘንድ መሣለቂያ እንደ ሆኑ ሙሴ አስተዋለ። 26ስለዚህ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ፣ “የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ ሌዋውያኑም ሁሉ ከርሱ ጋራ ሆኑ።
27ከዚያም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ ሰው በወገቡ ላይ ሰይፍ ይታጠቅ፤ በሰፈር ውስጥ ከዳር እዳር እየተመላለሰ እያንዳንዱ ወንድሙን፣ ጓደኛውንና ጎረቤቱን ይግደል’ ” አላቸው። 28ሌዋውያኑ ሙሴ እንዳዘዛቸው ፈጸሙ፤ በዚያም ዕለት ከሕዝቡ ሦስት ሺሕ ያህል ዐለቁ። 29ከዚያም ሙሴ፣ “በራሳችሁ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ላይ በመነሣታችሁ፣ በዛሬዋ ቀን ለእግዚአብሔር የተለያችሁ ሆናችኋል፤ በዛሬዋም ዕለት ባርኳችኋል” አለ።
30በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው።
31ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ። 32አሁን ግን አቤቱ ኀጢአታቸውን ይቅር በል፤ አለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እኔን ደምስሰኝ።”
33 እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የበደለኝን ሁሉ ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። 34አሁን ሂድ፤ ሕዝቡን ወደ ተናገርሁት ስፍራ ምራው፤ መልአኬም በፊትህ ይሄዳል፤ ሆኖም የምቀጣበት ጊዜ ሲደርስ፣ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።”
35አሮን በሠራው ጥጃ ባደረጉት ነገር እግዚአብሔር ሕዝቡን በመቅሠፍት መታ።

Currently Selected:

ዘፀአት 32: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ