ዘፀአት 34
34
አዲሶቹ የድንጋይ ጽላት
1 እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ጥረብ፤ እኔም አንተ በሰበርሃቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላት ላይ የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። 2በማለዳ ተዘጋጅተህ ወደ ሲና ተራራ ውጣ፤ በዚያ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም፤ 3ከአንተ ጋራ ማንም እንዳይመጣ ወይም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ፤ የበግና የፍየል መንጋዎች የቀንድ ከብቶችም እንኳ፣ በተራራው ፊት ለፊት መጋጥ የለባቸውም።”
4ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ጠርቦ፣ እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላትም በእጆቹ ያዘ። 5ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወረደ፤ በዚያም ከርሱ ጋራ ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን ዐወጀ። 6እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “እግዚአብሔር ርኅሩኅና ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ 7ፍቅርን ለሺሕዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”
8ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ 9“አቤቱ ጌታ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ ከእኛ ጋራ ይሂድ፤ ይህ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።”
10ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋራ ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው ዐብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደ ሆነ ያያሉ። 11ዛሬ የማዝዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ። 12ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል። 13መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ#34፥13 አሼራ የምትባለውን ጣዖት አምላክ ምስል ማለት ነው።፤ የአሼራ ዐጸዶቻቸውንም ቍረጡ። 14ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ።
15“በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ። 16ለወንዶች ልጆችህም ሴቶች ልጆቻቸውን ስታጭላቸውና እነዚህም ሴቶች ልጆች አምላኮቻቸውን በመከተል ሲያመነዝሩ፣ ወንዶች ልጆችህን ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሣሧቸዋል።
17“ቀልጠው የሚሠሩ አማልክትን አታብጅ።
18“የቂጣን በዓል አክብር። እንዳዘዝሁህም ለሰባት ቀን ቂጣ ብላ፤ ይህንም በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና።
19“የመንጋህ ወይም የበግና የፍየልህ፣ የቀንድ ከብትህ ተባዕት በኵር ሁሉ ሳይቀር፣ ከማሕፀን በኵር ሆኖ የሚወጣ ሁሉ የእኔ ነው። 20የአህያን በኵር በበግ ጠቦት ዋጀው፤ ካልዋጀኸው ግን ዐንገቱን ስበረው። በኵር ወንድ ልጆችህን ሁሉ ዋጅ።
“ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።
21“ስድስት ቀን ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍ፤ በዕርሻና በመከር ወቅት እንኳ ቢሆን ማረፍ አለብህ።
22“የሰባቱን ሱባዔ የመከር በዓል ከስንዴው መከር በኵራት ጋራ፣ እንዲሁም የመክተቻ በዓልን በዓመቱ መጨረሻ#34፥22 በዚያ አካባቢ ክረምት መግቢያ ላይ ማለት ነው። ላይ አክብር። 23በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ እግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። 24አሕዛብን ከፊትህ አስወጣለሁ፤ ድንበርህን አሰፋለሁ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ስትወጣ፣ ምድርህን ማንም አይመኝም።
25“እርሾ ካለው ከማንኛውም ነገር ጋራ የደም መሥዋዕት ለእኔ አታቅርብ፤ ከፋሲካ በዓል የተረፈው መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይቈይ።
26“የምድርህን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቤት አምጣ።
“ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።”
27ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው፤ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ከአንተና ከእስራኤል ጋራ ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና” አለው። 28ሙሴ እህል ሳይበላ፣ ውሃም ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር ጋራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዚያ ነበር፤ በጽላቱ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃሎች፣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጻፈ።
የሚያበራው የሙሴ ፊት
29ሙሴ ሁለቱን የምስክር ጽላት በእጆቹ ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋራ ከመነጋገሩ የተነሣ ፊቱ እንደሚያበራ አላወቀም ነበር። 30አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ባዩት ጊዜ ፊቱ ያበራ ነበር፤ ወደ እርሱ ለመቅረብም ፈርተው ነበር። 31ሙሴ ግን ጠራቸው፤ ስለዚህ አሮንና የማኅበሩ መሪዎች ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም አናገራቸው። 32ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔር በሲና ተራራ የሰጠውን ትእዛዞች ሁሉ ሰጣቸው።
33ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ። 34ሙሴም ከርሱ ጋራ ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ግን፣ እስከሚወጣ ድረስ መሸፈኛውን ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ የታዘዘውን ለእስራኤላውያን ነገራቸው። 35የእስራኤልም ልጆች ፊቱ የሚያበራ መሆኑን አዩ፤ ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋራ ለመነጋገር ተመልሶ እስኪሄድ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ በፊቱ ላይ ያደርግ ነበር።
Currently Selected:
ዘፀአት 34: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.