ዘፀአት 38

38
የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ
38፥1-7 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥1-8
1ከፍታው ሦስት ክንድ#38፥1 ርዝመቱ 1.4 ሜትር ያህል ማለት ነው። የሆነ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሠሩ#38፥1 ወይም ሥራ፤ ርዝመቱ ዐምስት ክንድ፣ ወርዱ ዐምስት ክንድ የሆነ ባለአራት ማእዘን ነበረ። 2ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ አራት ቀንድ ሠሩ፤ መሠዊያውንም በንሓስ ለበጡት። 3ዕቃዎቹንም ሁሉ ይኸውም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መርጫ ጐድጓዳ ሳሕኖቹን፣ ሜንጦዎቹንና የእሳት መያዣዎቹን ከንሓስ ሠሯቸው። 4ለመሠዊያውም ከጠርዝ በታች ሆኖ ከመሠዊያው ግማሽ ቁመት ላይ የሚሆን የንሓስ ፍርግርግ ማንደጃ ሠሩ። 5ለናሱ ፍርግርግ ማንደጃ አራት ማእዘኖች መሎጊያዎቹን እንዲይዙ የንሓስ ቀለበቶችን ሠሩ። 6መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠርተው በንሓስ ለበጧቸው። 7መሠዊያውን ለመሸከም በመሠዊያው ጐኖች ይሆኑ ዘንድ መሎጊያዎቹን በቀለበቶቹ ውስጥ አስገቧቸው፤ ውስጡንም ክፍት በማድረግ ከሳንቃዎች ሠሩት።
የመታጠቢያው ሳሕን
8የናስ መታጠቢያ ሳሕንና የንሓስ መቆሚያውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ከሚያገለግሉት ሴቶች መስተዋት ሠሩት።
አደባባዩ
38፥9-20 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥9-19
9ቀጥሎም አደባባዩን ሠሩ፤ የደቡቡ ክፍል ርዝመት አንድ መቶ ክንድ#38፥9 ወደ 45 ሜትር ያህል ነው። ሲሆን፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤ 10ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹ ላይ ዘንጎች ነበሩት። 11የሰሜኑም ክፍል ቁመቱ አንድ መቶ ክንድ ነበር፤ ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ነበሩት።
12የምዕራቡ ጫፍ ወርዱ ዐምሳ ክንድ#38፥12 ወደ 23 ሜትር ያህል ነው። ነበር፤ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች እንዲሁም የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ያሉት መጋረጃዎች ነበሩት። 13በፀሓይ መውጫ በኩል ያለው የምሥራቁም ጫፍ ወርዱ ዐምሳ ክንድ ነበር። 14ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋራ ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ#38፥14 ወደ 6.8 ሜትር ያህል ነው። የሆኑ መጋረጃዎች በአንድ በኩል ባለው መግቢያ ላይ ነበሩ፤ 15ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋራ ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ የሆኑ መጋረጃዎች በአደባባዩ መግቢያ በሌላው በኩል ነበሩ። 16በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ ነበሩ። 17የምሰሶዎቹ መቆሚያዎች ንሓስ ነበሩ፤ ኵላቦቹና በምሰሶዎቹ ላይ ያሉት ዘንጎች ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ ጫፎቻቸውም በብር ተለብጠው ነበር፤ ስለዚህ የአደባባዩ ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሯቸው።
18በአደባባዩ መግቢያ ላይ ያለው መጋረጃ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና የጥልፍ ባለሙያ ከጠለፈው፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠራ ነበር፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ#38፥18 ወደ 2.3 ሜትር ያህል ነው።፣ እንደ አደባባዩ መጋረጃዎች ከፍታው ዐምስት ክንድ ነበረ፤ 19አራት ምሰሶዎችና አራት መቆሚያዎች ነበሩት፤ ኵላቦቻቸውና ዘንጎቻቸው የብር ሲሆኑ፣ ጫፎቻቸው በብር ተለብጠው ነበር። 20የማደሪያው ድንኳንና የአደባባዩ ዙሪያ ካስማዎች ሁሉ ከንሓስ የተሠሩ ነበሩ።
ለአገልግሎት የዋሉ ዕቃዎች
21ለማደሪያው ድንኳን፣ ይኸውም ለምስክሩ ድንኳን ሙሴ ባዘዘው፣ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር መሪነት ሌዋውያኑ በጻፉት መሠረት የዕቃዎቹ ቍጥር ይህ ነው። 22ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ፣ የኡሪ ልጅ የሆነው ባስልኤል፣ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 23ከርሱም ጋራ ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ፣ ዕቅድ አውጭና የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ጥልፍ ጠላፊ ነበር። 24ለመቅደሱ ሥራ ሁሉ ከመወዝወዙ ስጦታ በመቅደሱ ሰቅል መሠረት የዋለው ጠቅላላ ወርቅ ሃያ ዘጠኝ መክሊትና ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል#38፥24 የወርቁ መጠን ወደ አንድ ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ነበረ።
25በቈጠራው ወቅት ተቈጥረው ከነበሩት ማኅበረ ሰብ የተገኘው ብር ለመቅደሱ ሰቅል አንድ መቶ መክሊትና አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሰባ ዐምስት ሰቅሎች#38፥25 የብሩ መጠን 20 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ነበሩ። 26ከተቈጠሩት ጋራ ዐብረው ከሆኑት ሃያና ከሃያ ዓመት በላይ የሆናቸው ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ሰዎች የሰጡት እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን በአንድ ሰው አንድ ቤካ ይኸውም ግማሽ ሰቅል#38፥26 ወደ 5.7 ግራም ያህል ነው። ነበረ። 27አንድ መቶ የብር መክሊቶች#38፥27 ወደ 3.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። የመቅደሱንና የመጋረጃዎቹን መቆሚያዎች ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር፤ ይኸውም ከአንድ መቶ መክሊቶች አንድ መቶ መቆሚያዎች ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ መቆሚያ አንድ መክሊት ማለት ነው። 28አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሰባ ዐምስት ሰቅሎችን#38፥28 ወደ 20 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ለምሰሶዎቹ ኵላቦች፣ የምሰሶዎቹን ዐናት ለመለበጥና ዘንጎቻቸውንም ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር።
29ከመወዝወዙ ስጦታ የሆነው ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺሕ አራት መቶ ሰቅል#38፥29 የናሱ መጠን 2.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ነበረ። 30ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ ለናስ መሠዊያው ከናስ መጫሪያው፣ ለዕቃዎቹም ሁሉ መቆሚያዎቹን ለመሥራት አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር፤ 31ለአደባባዩ ዙሪያ፣ ለመግቢያው እንዲሁም ለማደሪያው ድንኳን ካስማዎች ሁሉና ለአደባባዩ ዙሪያ ሁሉ እንዲሁ አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር።

Currently Selected:

ዘፀአት 38: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ