ዘፀአት 4
4
ለሙሴ የተሰጡ ምልክቶች
1ሙሴም “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” ብሎ መለሰ። 2እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “በእጅህ የያዝሃት እርሷ ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀው፤ እርሱም መልሶ፣ “በትር ናት” አለው።
3 እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “መሬት ላይ ጣላት” አለው።
ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ። 4እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደ ገና በትር ሆነች። 5እግዚአብሔርም (ያህዌ) “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው።
6 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ደግሞ፣ “እጅህን ብብትህ ውስጥ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ#4፥6 በዕብራይስጥ፣ ለምጽ የሚባለው ቈዳን ለሚያጠቁ በሽታዎች ሁሉ የሚውል እንጂ ቍምጥናን ወይም ለምጽን የሚያሳይ አይደለም። ሆነች።
7“አሁንም ደግሞ እጅህን ወደ ብብትህ መልሰህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን መልሶ ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ እንደ ገና እጁን ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ፣ ተመልሳ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነች።
8 እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “እንግዲህ ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ታምራዊ ምልክት ባይቀበሉ እንኳ ሁለተኛውን ያምናሉ። 9እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ወይም ቃልህን ባይቀበሉ ግን፣ ከአባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ቀድተህ በደረቅ ምድር ላይ አፍስሰው። ከወንዙም ቀድተህ ያፈሰስኸው ውሃ በምድር ላይ ደም ይሆናል።”
10ሙሴም እግዚአብሔርን (ያህዌ)፣ “ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው።
11 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አይደለሁምን? 12በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው። 13ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ (አዶናይ)፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው።
14በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል። 15ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ እረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። 16አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል። 17ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።”
ሙሴ ወደ ግብፅ ተመለሰ
18ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብፅ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው።
19ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው። 20ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብፅ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርንም (ኤሎሂም) በትር በእጁ ይዞ ነበር።
21 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብፅ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ። 22ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ 23ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ”
24ሙሴ#4፥24 ወይም፣ የሙሴ ልጅ ሊሆን ይችላል። ዕብራይስጡ፣ እርሱ ይላል። በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር። 25ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም#4፥25 ወይም ወደ ሙሴ እግር በመቅረብም ሊባል ይችላል። “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው። 26ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው።
27 እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አገኘው፤ ሳመውም። 28ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው።
29ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤ 30አሮንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። 31ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ የሚገድደው መሆኑንና መከራቸውን ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።
Currently Selected:
ዘፀአት 4: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.