ዘፀአት 6
6
1ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ፤ ከኀያሉ እጄ የተነሣ እንዲሄዱ ይለቅቃቸዋል፤ ከኀያሉም እጄ የተነሣ ከአገሩ ያስወጣቸዋል” አለው።
2እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3ሁሉን ቻይ አምላክ#6፥3 ዕብራይስጡ ኤልሻዳይ ይለዋል። ሆኜ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ ተገለጥሁላቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በተባለው ስሜ#6፥3 የዘፀ 3፥15 ማብ ይመ ራሴን አልገለጥሁላቸውም።#6፥3 ወይም እግዚአብሔር በተባለው ስሜ ራሴን አልገለጥሁላቸውምን? 4በእንግድነት የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር እንድሰጣቸው ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። 5ደግሞም በግብጻውያን ሥር በባርነት ሆነው ያሰሙትን የእስራኤላውያንን የሥቃይ ድምፅ ሰምቻለሁ ኪዳኔንም አስታውሻለሁ።
6“ስለዚህ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብጻውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ። 7የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ከግብጻውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ መሆኔንም ታውቃላችሁ። 8ከዚያም ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ እሰጣችኋለሁ ብዬ ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”
9ሙሴ ይህን ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ ተስፋ ከመቍረጣቸውና ከአስከፊ እስራታቸው የተነሣ ግን አላደመጡትም።
10ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 11“ሂድና ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን እስራኤላውያን ከአገሩ እንዲወጡ ይፈቅድላቸው ዘንድ ንገረው።”
12ሙሴ ግን እግዚአብሔርን፣ “እስራኤላውያን ያልሰሙኝ፣ ፈርዖን እንዴት ይሰማኛል፤ እኔ ለራሴ ተብታባ ሰው ነኝ”#6፥12 ዕብራይስጡ በዚህ ስፍራና በቍጥር 30 ላይ፣ ያልተገረዘ ከንፈር ይላል። አለው።
የሙሴና የአሮን የትውልድ መዝገብ
13በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ስለ እስራኤላውያንና ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ለሙሴና ለአሮን ነገራቸው፤ እስራኤላውያንንም ከግብጽ እንዲያወጡ አዘዛቸው።
14የየቤተ ሰቡ#6፥14 በዚህ ስፍራና በቍጥር 25 ላይ፣ ያለው ቤተ ሰብ የዕብራይስጥ ቃል ከጐሣም የበለጠ ነው። አለቆች እነዚህ ነበሩ፤
የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፣
ሄኖኅ፣ ፈሉስ፣ አስሮን፣ ከርሚ።
እነዚህ የሮቤል ነገድ ናቸው።
15የስምዖን ወንዶች ልጆች፣
ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሐርና የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል ነበሩ።
እነዚህ የስምዖን ነገድ አባቶች ናቸው።
16በትውልዳቸው መሠረት የሌዊ ወንዶች ልጆች ስሞች እነዚህ ነበሩ፤
ጌርሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ናቸው።
ሌዊ መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ።
17የጌርሶን ወንዶች ልጆች በትውልዳቸው ሎቤኒና ሰሜኢ ነበሩ።
18የቀዓት ወንዶች ልጆች
እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮንና ዑዝኤል ነበሩ፤
ቀዓት መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ኖረ።
19የሜራሪ ወንዶች ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ።
በትውልዳቸው መሠረት የሌዊ ነገዶች እነዚህ ናቸው።
20እንበረም የአጎቱን እናት ዮካብድን አገባ፤ እርሷም አሮንና ሙሴን ወለደችለት።
እንበረም መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ።
21የይስዓር ወንዶች ልጆች፣
ቆሬ፣ ናፌግና ዝክሪ ነበሩ።
22የዑዝኤል ወንዶች ልጆች፣
ሚሳኤል፣ ኤልዳፋንና ሥትሪ ነበሩ።
23አሮንም የአሚናዳብን ልጅ፣ የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፤ እርሷም ናዳብንና አብዩድን፣ አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት።
24የቆሬ ወንዶች ልጆች፣
አሴር፣ ሕልቃናና አብያሳፍ ነበሩ፤
እነዚህ የቆሬ ነገድ ጐሣ ናቸው።
25የአሮን ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ሴት ልጆች አንዷን አገባ፤ እርሷም ፊንሐስን ወለደችለት።
እነዚህ እንደየነገዳቸው የሌዋውያን ጐሣዎች አለቆች ነበሩ።
26 እግዚአብሔር “እስራኤላውያንን በየሰራዊታቸው ከግብጽ አውጡ” ብሎ የነገራቸው አሮንንና ሙሴን ነበር። 27ስለ እስራኤላውያን ከግብጽ መውጣት፣ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን ያናገሩትም እነዚሁ ሙሴና አሮን ነበሩ።
28 እግዚአብሔር ሙሴን በግብጽ በተናገረው ጊዜ፣ 29እንዲህ አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የነገርሁህን ሁሉ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው።”
30ሙሴ ግን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ፈርዖን ምን ብሎ ይሰማኛል? አንደበቴ ኰልታፋ ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.