ዘፀአት 7

7
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ልብ በል፤ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህ አሮንም ያንተ ነቢይ ይሆናል። 2እኔ የማዝህን ሁሉ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም እስራኤላውያንን ከአገሩ እንዲወጡ ይለቅቃቸው ዘንድ ለፈርዖን ይነግረዋል። 3እኔ ግን የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፤ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በግብጽ ላይ በብዛት ባደርግም እንኳ፣ አይሰማችሁም። 4ከዚያም እጄን በግብጽ ላይ አደርጋለሁ፤ በኀያል ፍርድም ሰራዊቴን፣ ሕዝቤን እስራኤላውያንን አወጣለሁ። 5እጄን በግብጽ ላይ ስዘረጋና እስራኤላውያንንም ከዚያ ሳወጣ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”
6ሙሴና አሮን እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው አደረጉ። 7ፈርዖንን ባነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት፣ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ነበር።
የአሮን በትር እባብ ሆነች
8 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፣ 9“ፈርዖን፣ ‘ታምር አሳዩኝ’ ባላችሁ ጊዜ፣ አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በትርህን ውሰድና በፈርዖን ፊት ጣላት፤’ ከዚያም እባብ ትሆናለች።”
10ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮን በትሩን በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት ጣላት፤ እባብም ሆነች። 11ከዚያም ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ የግብጽ አስማተኞችም በድብቅ ጥበባቸው ያንኑ አደረጉ፤ 12እያንዳንዱ የያዛትን በትር ጣለ፤ እባብም ሆነች። ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ዋጠች። 13ሆኖም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር ተናግሮ እንደ ነበረውም አላደመጣቸውም።
የደም መቅሠፍት
14ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡን ለመልቀቅ አልፈቀደም። 15ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ። 16ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ ዕሺ አላልህም። 17እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ! በዚህች በእጄ በያዝኋት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ፤ ወደ ደምም ይለወጣል። 18በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብጻውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።” ’ ”
19 እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብጽ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኵሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከዕንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብጽ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።”
20ሙሴና አሮን እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ፤ ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ። 21በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብጻውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብጽ ምድር ሁሉ ደም ነበረ።
22የግብጽ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም። 23ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህን ከቁም ነገር አልቈጠረውም። 24ግብጻውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጕድጓድ ቈፈሩ።
25 እግዚአብሔር አባይን ከመታ ሰባት ቀን ሞላ።

Currently Selected:

ዘፀአት 7: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ