ሕዝቅኤል 14
14
ባዕድ አምልኮ ተከታዮች መወገዛቸው
1ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። 2ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 3“የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን? 4ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ። 5በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’
6“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ!
7“ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ። 8ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
9“ ‘ነቢዩ ትንቢት ይናገር ዘንድ ቢታለል፣ ያን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ክንዴን በርሱ ላይ አነሣለሁ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከልም አጠፋዋለሁ። 10በደላቸው በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ነቢዩም እርሱን ሊጠይቀው ከመጣው ሰው ጋራ እኩል በደለኛ ይሆናል። 11ከእንግዲህ የእስራኤል ሕዝብ መንገድ ስቶ ከእኔ አይለይም፤ ተመልሶም በኀጢአቱ ሁሉ ራሱን አያረክስም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”
የማያመልጡት ፍርድ
12ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 13“የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ አገር በእኔ ባለ መታመን ቢበድለኝና እኔም እጄን በላዩ ዘርግቼ የምግብ ምንጩን ባደርቅ፣ ራብንም አምጥቼበት ሰውንና እንስሳቱን ብገድል፣ 14ኖኅ፣ ዳንኤልና#14፥14 የዕብራይስጡን ቃል አጻጻፍ ስንመለከት ነቢዩን ዳንኤልን ሳይሆን፣ ተመሳሳይ ስም ያለውን ሌላ ሰው የሚያመለክት ይመስላል 20። ኢዮብ እነዚህ ሦስቱ በዚያ ቢኖሩ እንኳ፣ በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15“የዱር አራዊትንም በአገሪቱ ላይ ሰድጄ፣ አገሪቱን ሕፃናት አልባ ቢያደርጓትና ከአራዊቱም የተነሣ ምድሪቱ ሰው እስከማያልፍባት ባድማ ብትሆን፣ 16‘በሕያውነቴ እምላለሁ!’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ቢኖሩባት እንኳ፣ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም፤ እነርሱ ብቻ ይድናሉ፤ ምድሪቱ ግን ባድማ ትሆናለች።
17“ሰይፍን በአገሪቱ ላይ አምጥቼ፣ ‘ሰይፍ በዚህ ምድር ይለፍ’ ብል፣ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣ 18በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባትም እንኳ ራሳቸው ብቻ ይድናሉ እንጂ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም።
19“ቸነፈርንም በምድሪቱ ላይ ብሰድድና ደም በማፍሰስ መዓቴን አውርጄ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣ 20በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ቢኖሩባትም እንኳ፣ በጽድቃቸው ራሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችን ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም።
21“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ሰውንና እንስሳቱን ለማጥፋት አራቱን አስፈሪ ፍርዶቼን፦ ሰይፍን፣ ራብን፣ የዱር አራዊትንና ቸነፈርን በኢየሩሳሌም ላይ በማመጣበት ጊዜ ምንኛ የከፋ ይሆን! 22ነገር ግን ከዚያ ወጥተው የሚተርፉ ወንዶችና ሴቶች ልጆች አሉ፤ እነርሱም ወደ እናንተ ይመጣሉ፤ እናንተም አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ፣ በኢየሩሳሌም ላይ ስላመጣሁት መከራ፣ ስላደረስሁባትም አስከፊ ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ። 23አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ፣ ትጽናናላችሁ፤ አንዳች ነገር በከንቱ እንዳላደረገሁ ትረዳላችሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 14: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.