ሕዝቅኤል 17
17
የንስሮቹና የወይኑ ምሳሌ
1ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ዕንቈቅልሽ አቅርብ፤ ለእስራኤልም ቤት በተምሳሌት ተናገር፤ 3እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትልቅ ክንፍና ረዥም ማርገብገቢያ ያለው እንዲሁም አካሉ በላባ የተሸፈነ መልኩ ዝንጕርጕር የሆነ ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጥቶ የዝግባ ዛፍ ጫፍ ያዘ፤ 4ከጫፉም የላይኛውን ቀንበጥ ቀንጥቦ ወደ ነጋዴዎች ምድር ወሰደ፤ በሸቀጥ ነጋዴዎችም ከተማ ተከለው።
5“ ‘ከዚህ በኋላ ከምድሪቱ ዘር ወስዶ በመልካም ዐፈር አኖረው፤ ውሃ እንደ ልብ ባለበት ቦታ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ ተከለው፤ 6በበቀለም ጊዜ ዐጭርና ወደ ጐን የተንሰራፋ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎቹም ወደ እርሱ አቅጣጫ ዐደጉ፤ ሥሮቹ ግን እዚያው ከበታቹ ቀሩ። ስለዚህ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎችን አወጣ፤ ለምለም ቅጠሎችንም አበቀለ።
7“ ‘ደግሞም ትልቅ ክንፍ ያለውና አካሉ በላባ የተሸፈነ ሌላ ታላቅ ንስር ነበር። ያ የወይን ተክልም ውሃ ለማግኘት ከተተከለበት ቦታ ሥሩን ወደ እርሱ ሰደደ፤ ቅርንጫፉንም ወደ እርሱ ዘረጋ። 8ቅርንጫፍ እንዲያወጣ፣ ፍሬ እንዲያፈራና ያማረ የወይን ተክል እንዲሆን በአጠገቡ ብዙ ውሃ ባለበት በመልካም መሬት ተተክሎ ነበር።’
9“እንዲህም በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያድግ ይሆን? ይጠወልግ ዘንድ ሥሩ ተነቅሎ ፍሬው አይረግፍምን? ቀንበጡም ሁሉ ይደርቃል። ከሥሩ ለመንቀል ብርቱ ክንድና የብዙ ሰው ጕልበት አያስፈልገውም። 10በሌላ ስፍራ ቢተከልስ ይጸድቅ ይሆን? የምሥራቅ ነፋስ ሲመታውስ ባደገበት ስፍራ ፈጽሞ አይደርቅምን?’ ”
11ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 12“ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ በል፤ ‘የእነዚህ ነገሮች ትርጕም ምን እንደ ሆነ አታውቁምን?’ እንዲህ በላቸው፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ንጉሧንና መሳፍንቷን ማረከ፤ ወደ ባቢሎንም ይዟቸው ተመለሰ። 13ከንጉሣውያን ቤተ ሰብ አንዱን ወስዶ ከርሱ ጋራ ውል አደረገ፤ በመሐላም ቃል አስገባው፤ የምድሪቱንም ታላላቅ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፤ 14ይኸውም የምድሪቱ መንግሥት ተዋርዳ የርሱን ውል በመጠበቅ ብቻ እንድትኖር እንጂ፣ ዳግመኛ እንዳታንሰራራ ለማድረግ ነበር። 15ንጉሡ ግን በርሱ ላይ ዐመፀ፤ ፈረሶችና ብዙ ሰራዊት ለማግኘት መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ፤ ይሳካለት ይሆን? እንዲህ ዐይነቱን ነገር የፈጸመ ያመልጣልን? ውል ያፈረሰስ ሳይቀጣ ይቀራልን?
16“ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ መሐላውን ባቀለለበት፣ ውሉን ባፈረሰበት፣ በዙፋንም ላይ ባስቀመጠው ንጉሥ ምድር በባቢሎን ይሞታል። 17በባቢሎናውያን ብዙ ሕይወት ለማጥፋት በከተማዪቱ ዙሪያ ዐፈር በሚደለድሉበትና ምሽግ በሚሠሩበት ጊዜ፣ ፈርዖን ከኀያል ሰራዊቱና ከብዙ ጭፍሮቹ ጋራ በጦርነት ሊረዳው አይችልም። 18ያደረገውን መሐላ በማቃለልና እጁን ያስገባበትን ውል በማፍረስ ይህን ሁሉ ስለ ፈጸመ ከቅጣት አያመልጥም።
19“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ ያቃለለውን መሐላዬንና ያፈረሰውን ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ። 20መረቤን በላዩ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል። ወደ ባቢሎን እወስደዋለሁ፤ በእኔ ላይ ስላመፀም በዚያ እፈርድበታለሁ። 21የሚሸሸው ወታደሩ ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል፤ የተረፉትም ወደ ነፋስ ይበተናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።
22“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ እኔው ራሴ ቀንበጡን ወስጄ እተክለዋለሁ፤ ከቀንበጦቹ ጫፍ አንዱን ቀንጥሼ ከሁሉ ከፍ ባለው ተራራ ላይ እተክለዋለሁ። 23ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፤ ቅርንጫፎች ያወጣል፤ ፍሬ ያፈራል፤ ያማረም ዝግባ ይሆናል። የወፍ ዐይነት ሁሉ መኖሪያውን በዚያ ያደርጋል፤ በቅርንጫፎቹም ጥላ ሥር ያርፋል። 24የዱር ዛፎች ሁሉ ረዥሙን ዛፍ፣ ዝቅ ዝቅ ያለውንም ዛፍ ከፍ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ የለመለመውን ዛፍ አደርቃለሁ፤ ደረቁንም አለመልማለሁ።
“ ‘እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እኔው አደርገዋለሁ።’ ”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.