ሕዝቅኤል 26
26
በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት
1በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ጢሮስ ስለ ኢየሩሳሌም፣ ‘ዕሠይ! የሕዝቦች በር ተሰበረች፤ ደጆቿም ወለል ብለው ተከፈቱልኝ፤ እንግዲህ እርሷ ስለ ፈራረሰች እኔ እከብራለሁ’ ብላለችና፤ 3ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ጢሮስ ሆይ፤ እነሆ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ባሕር ሞገዷን እንደምታስነሣ፣ ብዙ ሕዝብ አስነሣብሻለሁ። 4የጢሮስን ቅጥሮች ያወድማሉ፤ ምሽጎቿንም ያፈርሳሉ። ዐፈሯን ከላይዋ ጠርጌ የተራቈተ ዐለት አደርጋታለሁ። 5እኔ ጌታ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፤ በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆናለች፤ አሕዛብም ይበዘብዟታል፤ 6መኻል አገር ያሉ ሰፈሮቿም በሰይፍ ይወድማሉ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’
7“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን#26፥7 በዕብራይስጥ ናቡከደነፆር የሚለው ቃል አማራጭ ትርጕም ናቡካድረፃር ነው፤ በዚህ ክፍልና በአብዛኛው በሕዝቅኤልና በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ እንደዚሁ ነው። ከፈረሶችና ከሠረገሎች ጋራ፣ ከፈረሰኞችና ከታላቅ ሰራዊትም ጋራ ከሰሜን በጢሮስ ላይ አመጣለሁ። 8እርሱ መኻል አገር ያሉ ሰፈሮችሽን በሰይፍ ያወድማቸዋል፤ በዙሪያሽ ካብ ይክባል፤ እስከ ቅጥሮችሽ ጫፍ ድረስ ዐፈር ይደለድልብሻል፤ ጋሻውንም በአንቺ ላይ ያነሣል። 9ግንብ መደርመሻውን በቅጥሮቿ ላይ ያነጣጥራል፤ በመሣሪያም ምሽጎችሽን ያፈርሳል። 10ከፈረሶቹ ብዛት የተነሣ ዐቧራ ይሸፍንሻል፤ ሰዎች ቅጥሮቿ ወደ ፈረሱ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ፣ ከፈረሶቹና ከጋሪዎቹ፣ ከሠረገሎቹም ድምፅ የተነሣ ቅጥሮችሽ ይናወጣሉ። 11መንገዶችሽ ሁሉ በፈረሶቹ ኰቴ ይረጋገጣሉ፤ ሕዝብሽን በሰይፍ ይገድላል፤ ታላላቅ ምሰሶዎችሽ ወደ ምድር ይወድቃሉ። 12ሀብትሽን ይዘርፋሉ፤ ሸቀጥሽን ይበዘብዛሉ፤ ቅጥሮችሽን ያፈርሳሉ፤ የተዋቡ ቤቶችሽን ያወድማሉ፤ ድንጋይሽን፣ ዕንጨትሽንና የግንቦች ፍርስራሽ ወደ ባሕር ይጥላሉ። 13ዘፈንሽን ጸጥ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም የበገናሽ ድምፅ አይሰማም። 14የተራቈተ ዐለት አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆኛለሽ፤ እንደ ገናም ተመልሰሽ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’
15“ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላል፤ ‘የቈሰሉት ሲያቃስቱ፣ በውስጥሽም ጭፍጨፋ ሲካሄድ፣ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች አይነዋወጡምን? 16የባሕር ጠረፍ መሳፍንት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ይጥላሉ፤ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውን ያወልቃሉ። ፍርሀት ተከናንበው በመሬት ላይ በመቀመጥ ባለማቋረጥ፣ እየተንቀጠቀጡ በአንቺ ላይ በደረሰው ነገር ይሸበራሉ፤’ 17ስለ አንቺም እንዲህ ብለው ሙሾ ያወርዳሉ፤
“ ‘በባሕር ሰዎች የሚኖሩብሽ፣
ባለዝናዋ ከተማ ሆይ፤ እንዴት ጠፋሽ!
ከነዋሪዎችሽ ጋራ፣
የባሕር ላይ ኀያል ነበርሽ፤
በዚያ በሚኖሩትም ሁሉ ዘንድ
የተፈራሽ ነበርሽ።
18አሁን በመውደቂያሽ ቀን፣
በጠረፍ ያሉ አገሮች ተናወጡ፤
ከመፍረስሽም የተነሣ፤
በባሕር ውስጥ ያሉ ደሴቶች ተደናገጡ።’
19“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች ባድማ ሳደርግሽ፣ የውቅያኖስንም ውሃ በላይሽ አድርጌ በቀላይ ስሸፍንሽ፣ 20የጥንት ዘመን ሰዎች ወደ ገቡበት ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ አወርድሻለሁ፤ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ በጥንቱ ፍርስራሽ ከምድር በታች አኖርሻለሁ፤ ከዚህም በኋላ በሕያዋን ምድር ተመልሰሽ ቦታ አታገኚም፤#26፥20 ከሰብዐ ሊቃናት ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን፣ ዕብራይስጡ ግን ተመለሱ፤ ክብርን እሰጣለሁ ይላል። 21መጨረሻሽን አሳዛኝ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊያለሽ፤ ከቶም አትገኚም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 26: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.