ሕዝቅኤል 3

3
1እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በፊትህ ያለውን ብላ፤ ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላና ሄደህ ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ። 2ስለዚህ አፌን ከፈትሁ፤ እርሱም መጽሐፉን አጐረሠኝ።
3እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምሰጥህን ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላ፤ ሆድህንም ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠኝ።
4እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፤ ቃሌንም ንገራቸው። 5ወደ እስራኤል ቤት እንጂ፣ ንግግሩ ወደማይገባና ቋንቋው ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህም፤ 6ንግግራቸው ወደማይገባና ቋንቋቸው ወደማይታወቅ፣ ቃላቸውንም መረዳት ወደማይቻልህ ብዙ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥ ይሰሙህ ነበር። 7ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለ ሆኑ ሊሰሙኝ አልፈለጉም፤ ስለዚህ የእስራኤል ቤት አንተንም አይሰሙህም። 8እነሆ እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ። 9ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር አልማዝ አደርገዋለሁ። ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም እንኳ አትፍራቸው፤ በፊታቸውም አትሸበር።”
10እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የምነግርህን ቃል ሁሉ በጥንቃቄ አድምጥ፤ በልብህም ያዝ። 11ተነሥተህም በምርኮ ወዳሉት ወገኖችህ ሄደህ ተናገራቸው፤ ቢሰሙህም ባይሰሙህም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ በላቸው።”
12መንፈስም ወደ ላይ ከፍ አድርጎ አነሣኝ፤ ከኋላዬም፣ “የእግዚአብሔር ክብር በማደሪያ ስፍራው ይባረክ!” የሚል ታላቅ ህምህምታ ሰማሁ፤ 13ይህም የሕያዋኑ ፍጡራን ክንፎች እርስ በርስ ሲጋጩና በአጠገባቸው ያሉት መንኰራኵሮች የሚያሰሙት ታላቅ ህምህምታ ነበር። 14መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ወሰደኝ፤ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቍጣ ሄድሁ፤ የእግዚአብሔርም ጽኑ እጅ በላዬ ነበረች። 15ከዚያም በኮቦር ወንዝ አጠገብ በቴልአቢብ ወደሚኖሩት ምርኮኞች መጣሁ፣ በድንጋጤ ፈዝዤም ከእነርሱ ጋራ ሰባት ቀን በመካከላቸው ተቀመጥሁ።
ለእስራኤል የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
16ከሰባቱም ቀን በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 17“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ የምነግርህንም ማስጠንቀቂያ አስተላልፍላቸው። 18ኀጢአተኛውን ሰው፣ ‘በርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ አንተ ባታስጠነቅቀው፣ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባትነግረው፣ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ#3፥18 ወይም ስለ ኀጢአቱ፤ እንዲሁም 19 እና 20 ይመ ይሞታል፤ አንተን ግን ስለ ደሙ እጠይቅሃለሁ። 19ነገር ግን ክፉውን ሰው አስጠንቅቀኸው፣ ከኀጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ እርሱ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ።
20“ጻድቁ ሰው ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ እኔም መሰናክል በፊቱ ባስቀምጥ እርሱ ይሞታል፤ አንተ አላስጠነቀቅኸውምና በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረገውም ጽድቅ አይታሰብለትም፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ። 21ነገር ግን ጻድቁን ሰው ኀጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀውና እርሱም ኀጢአትን ባይሠራ፣ ተጠንቅቋልና በርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን ታድናለህ።”
22እግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም፣ “ተነሥተህ ወደ ረባዳው ስፍራ ሂድ፤ በዚያ እናገርሃለሁ” አለኝ። 23እኔም ተነሥቼ ወደ ረባዳው ስፍራ ሄድሁ። በኮቦር ወንዝ አጠገብ ያየሁት ዐይነት ክብር፣ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ።
24መንፈስ በውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ እንዲህም ሲል ተናገረኝ፤ “ሂድ፤ ቤትህ ገብተህ በርህን ዝጋ። 25አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ በገመድ ይጠፍሩሃል፤ ወጥተህም በሕዝብ መካከል እንዳትመላለስ ያስሩሃል። 26ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ልትገሥጻቸው እንዳትችል ምላስህን ከላንቃህ ጋራ አጣብቃለሁ፤ ድዳም ትሆናለህ። 27ነገር ግን በምናገርህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፤ አንተም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ትላቸዋለህ። የሚሰማ ይስማ፤ የማይሰማም አይስማ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 3: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ