ሕዝቅኤል 31
31
የሊባኖስ ዝግባ
1በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖንና ስፍር ቍጥር ለሌለው ሕዝቡ እንዲህ በል፤
“ ‘በክብር ከአንተ ጋራ ማን ሊወዳደር ይችላል?
3ለጫካው ጥላ የሆኑ የሚያማምሩ ቅርንጫፎች የነበሩትን፣
እጅግ መለሎ ሆኖ፣
ጫፉ ሰማይ የደረሰውን፣
የሊባኖስን ዝግባ አሦርን ተመልከት።
4ውሆች አበቀሉት፤
ጥልቅ ምንጮች አሳደጉት፤
ጅረቶቻቸው ፈሰሱ፤
የሥሮቹንም ዙሪያ ሁሉ አረሰረሱ፤
በመስኩ ላይ ወዳሉት ዛፎች ሁሉ፣
መስኖዎቻቸውን ለቀቁት።
5ስለዚህ በደን ካሉት ዛፎች ሁሉ፣
እጅግ ከፍ አለ፤
ቅርንጫፎቹ በዙ፤
ቀንበጦቹ ረዘሙ፤
ከውሃውም ብዛት የተነሣ ተስፋፉ።
6የሰማይ ወፎች ሁሉ፣
በቅርንጫፎቹ ላይ ጐጇቸውን ሠሩ፤
የምድር አራዊት ሁሉ፣
ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ።
ታላላቅ መንግሥታትም ሁሉ፣
ከጥላው ሥር ኖሩ።
7ከተንሰራፉት ቅርንጫፎቹ ጋራ፣
ውበቱ ግሩም ነበር፤
ብዙ ውሃ ወዳለበት፣
ሥሮቹ ጠልቀው ነበርና።
8በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ ያሉ ዝግባዎች፣
ሊወዳደሩት አልቻሉም፤
የጥድ ዛፎች፣
የርሱን ቅርንጫፎች አይተካከሉትም፤
የኤርሞን ዛፎችም፣
ከርሱ ቅርንጫፎች ጋራ አይወዳደሩም፤
በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣
በውበት አይደርስበትም።
9በብዙ ቅርንጫፎች፣
ውብ አድርጌ ሠራሁት፤
በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ፣
በዔድን ያሉትን ዛፎች የሚያስቀና አደረግሁት።
10“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጥቅጥቅ ባለው ቅጠል ላይ ጫፉን ከፍ በማድረግ ራሱን በማንጠራራቱ፣ በርዝማኔውም በመኵራራቱ፣ 11እንደ ክፋቱ መጠን የሥራውን ይከፍለው ዘንድ፣ ለአሕዛብ ገዥ አሳልፌ ሰጠሁት። አውጥቼ ጥዬዋለሁ፤ 12ከአሕዛብ ወገን እጅግ ጨካኝ የሆኑትም ባዕዳን ሰዎች ቈራርጠው ጣሉት። ቀንበጦቹ በተራራዎቹና በሸለቆዎቹ ሁሉ ላይ ወድቀዋል፤ ቅርንጫፎቹም በውሃ መውረጃዎቹ ሁሉ ላይ ተሰባብረው ወድቀዋል፤ የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ከጥላው ሥር በመውጣት ትተዉት ሄደዋል። 13የሰማይ ወፎች ሁሉ በወደቀው ዛፍ ላይ ሰፈሩ፤ የምድር አራዊት ሁሉ በወደቀው ዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ሰፈሩ። 14ስለዚህ በውሃ አጠገብ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣ ጫፎቹን ችምችም ካለው ቅጠል በላይ ከፍ በማድረግ፣ ከእንግዲህ ራሱን በትዕቢት አያንጠራራም። ከእንግዲህ ውሃ በሚገባ ያገኘ ማንኛውም ዛፍ ወደዚህ ዐይነቱ ከፍታ አይደርስም። ሁሉም ከምድር በታች ወደ ጕድጓድ ከሚወርድ ሟች ጋራ ዐብሮ እንዲሞት ተወስኖበታልና።
15“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ መቃብር#31፥15 ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል፤ እንዲሁም በ16 እና 17 በወረደበት ቀን ጥልቅ ምንጮችን ስለ እርሱ በሐዘን ሸፈንኋቸው፤ ወንዞቹን ገታሁ፤ ታላላቅ ፈሳሾችም ተቋረጡ። በርሱም ምክንያት ሊባኖስን ጨለማ አለበስሁ፤ የደን ዛፎችም ሁሉ ደረቁ። 16ወደ ጕድጓድ ከሚሄዱት ጋራ ወደ መቃብር ባወረድሁት ጊዜ ሲወድቅ በተሰማው ድምፅ አሕዛብ ደነገጡ። ከዚያም የዔድን ዛፎች ሁሉ፣ ምርጥና ልዩ የሆኑት የሊባኖስ ዛፎች፣ ውሃ የጠገቡትም ዛፎች ሁሉ ከምድር በታች ሆነው ተጽናኑ። 17ከአሕዛብ መካከል ከርሱ ጋራ ያበሩ፣ በጥላው ሥር የኖሩ፣ በሰይፍ ከሞቱት ጋራ ለመቀላቀል ወደ መቃብር ወርደዋል።
18“ ‘በዔድን ካሉት ዛፎች በውበትና በትልቅነት የሚወዳደርህ የትኛው ነው? ይሁን እንጂ አንተም እንደዚሁ ከዔድን ዛፎች ጋራ ከመሬት በታች ትወርዳለህ፤ በሰይፍ ከተገደሉት፣ ካልተገረዙትም መካከል ትጋደማለህ።
“ ‘እንግዲህ ፈርዖንና ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝቡ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 31: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.