ገላትያ 3
3
እምነት ወይስ የኦሪትን ሕግ መጠበቅ
1እናንተ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! ለመሆኑ ማን መተት አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊት ለፊታችሁ በግልጽ ተሥሎ ነበር። 2ከእናንተ ዘንድ አንድ ነገር ብቻ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ መንፈስን የተቀበላችሁት ሕግን በመጠበቅ ነው ወይስ የተሰበከላችሁን በማመን? 3ይህን ያህል የማታስተውሉ ናችሁን? በመንፈስ ጀምራችሁ በሥጋ#3፥3 እንደዚህ ባለ ዐውድ ውስጥ ሥጋ የሚለው ቃል የሚያመላክተው ኀጢአተኛ የሆነና የመንፈስን ሥራ የሚቃወመውን ማንነት ነው። ፍጹም ለመሆን ትጥራላችሁን? 4በርግጥ ለከንቱ ከሆነ፣ ይህን ያህል መከራ የተቀበላችሁት እንዲያው ነውን? 5እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁ፣ በእናንተም ዘንድ ታምራትን የሚሠራው ሕግን ስለ ጠበቃችሁ ነው ወይስ የሰማችሁትን ስላመናችሁ? 6ልክ እንደዚሁ፣ አብርሃም “እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።”#3፥6 ዘፍ 15፥6
7እንግዲህ እነዚያ የሚያምኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ አስተውሉ። 8መጽሐፍ፣ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ በማየት፣ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ”#3፥8 ዘፍ 12፥3፤ 18፥18፤ 22፥18 በማለት ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታወቀው። 9ስለዚህ በእምነት የሆኑት፣ የእምነት ሰው ከሆነው ከአብርሃም ጋራ ቡሩካን ናቸው።
10ሕግን በመጠበቅ የሚተማመኑ ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ የማያደርግ የተረገመ ነው”#3፥10 ዘዳ 27፥26 ተብሎ ተጽፏልና። 11“ጻድቅ በእምነት ይኖራል”#3፥11 ዕን 2፥4 ስለ ተባለ፣ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው። 12ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ነገር ግን “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ሕያው ይሆናል”#3፥12 ዘሌ 18፥5 ተብሏል። 13“በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው”#3፥13 ዘዳ 21፥23 ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል። 14ለአብርሃም የተሰጠው በረከት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ለአሕዛብ እንዲደርስ ዋጅቶናል፤ ይኸውም በእምነት የመንፈስን ተስፋ እንድንቀበል ነው።
የኦሪት ሕግና የተስፋ ቃል
15ወንድሞች ሆይ፤ ከሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደውን ምሳሌ አድርጌ ላቅርብ፤ የሰው ኪዳን እንኳ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም በርሱ ላይ ሊጨምርበት እንደማይችል ሁሉ፣ በዚህም ጕዳይ ቢሆን እንደዚሁ ነው። 16የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ”#3፥16 ዘፍ 12፥7፤ 13፥15፤ 24፥7 አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። 17የምለው እንዲህ ነው፦ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ፣ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የጸናውን ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም። 18ርስትን መውረስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፣ በተስፋ ቃል ባልተገኘ ነበርና፤ እግዚአብሔር ግን በጸጋው በተስፋ ቃል አማካይነት ለአብርሃም ሰጥቶታል።
19ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ ነበር። 20ሆኖም መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
21ታዲያ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? ከቶ አይሆንም! ሕግ የተሰጠው ሕይወትን ለማስገኘት ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥም ጽድቅ በሕግ በኩል በተገኘ ነበር። 22መጽሐፍ ግን ዓለም ሁሉ የኀጢአት እስረኛ መሆኑን ያውጃል፤ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው ተስፋ ለሚያምኑት ሁሉ ይሰጥ ዘንድ ነው።
የእግዚአብሔር ልጆች
23ይህ እምነት ከመምጣቱ በፊት በሕግ አማካይነት እስረኞች ሆነን፣ እምነት እስከሚገለጥ ድረስ ተዘግቶብን ነበር። 24ስለዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰን#3፥24 ወይም ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ሞግዚታችን ሆነ። 25አሁን ግን ያ እምነት ስለ መጣ፣ ከእንግዲህ በሕግ ሞግዚትነት ሥር አይደለንም።
26ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ 27ከክርስቶስ ጋራ አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና። 28በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነጻ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፤ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ። 29የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።
Currently Selected:
ገላትያ 3: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.