ዘፍጥረት 22

22
አብርሃም ተፈተነ
1ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው።
እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ።
2እግዚአብሔርም፣ “የምትወድደውን አንዱን ልጅህን፣ ይሥሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው።
3በማግስቱም ጧት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይሥሐቅን ይዞ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጕዞውን ጀመረ፤ 4በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤ 5አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው።
6አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይሥሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም ዐብረው ሄዱ። 7ይሥሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው።
አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው።
ይሥሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት በግ የት አለ?” ብሎ ጠየቀ።
8አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” አለው። ሁለቱም ዐብረው ጕዟቸውን ቀጠሉ።
9እግዚአብሔር ወደ አመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይሥሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው። 10ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ። 11እግዚአብሔር መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም! አብርሃም!” ብሎ ጠራው።
አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።
12እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና” አለው።
13አብርሃም ቀና ብሎ ተመለከተ፤ በቍጥቋጦ መካከልም ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። 14ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል።
15እግዚአብሔርም መልአክ አብርሃምን ከሰማይ ዳግመኛ ጠራው፤ 16እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና፣ 17በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ 18አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና።”
19ከዚያም አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተያይዘውም ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ኖረ።
የናኮር ልጆች
20ከዚህ በኋላ እንዲህ ተብሎ ለአብርሃም ተነገረው፤ “ሚልካም ደግሞ የልጆች እናት ሆናለች፤ ለወንድምህም ለናኮር ወንዶች ልጆችን ወልዳለች።
21እነርሱም የበኵር ልጁ ዑፅና ወንድሙ ቡዝ፣
የአራም አባት ቀሙኤል፣
22ኮዛት፣ ሐዞ፣ ፊልዳሥ፣ የድላፍና ባቱኤል ናቸው።”
23ባቱኤልም ርብቃን ወለደ።
ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር የወለደችለት እነዚህ ስምንት ወንዶች ልጆች ናቸው።
24ከእነዚህም ሌላ የናኮር ቁባት ሬናሕ ደግሞ ጥባሕ፣ ገአም፣ ተሐሽና ሞክሳ የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 22: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ