ዘፍጥረት 25
25
የአብርሃም መሞት
25፥1-4 ተጓ ምብ – 1ዜና 1፥32-33
1አብርሃም ኬጡራ የተባለች ሌላ ሚስት አገባ።#25፥1 ወይም አግብቶ ነበር 2እርሷም፦ ዘምራንን፣ ዮቅሳንን፣ ሜዳንን፣ ምድያምን፣ የስቦቅንና ስዌሕን ወለደችለት። 3ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ፤ የድዳንም ልጆች፦ አሦራውያን፣ ለጡሳውያንና ለኡማውያን ናቸው። 4የምድያም ልጆች፦ ጌፌር፣ ዔፌር፣ ሄኖኅ፣ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው።
5አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይሥሐቅ አወረሰው፤ 6ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው፤ ከልጁ ከይሥሐቅም ርቀው እንዲኖሩ ወደ ምሥራቅ ምድር ሰደዳቸው።
7አብርሃም በጠቅላላው መቶ ሰባ ዐምስት ዓመት ኖረ። 8ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 9ልጆቹ ይሥሐቅና እስማኤል በመምሬ አጠገብ በምትገኝ በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን ዕርሻ በመክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤ 10ይህም የዕርሻ ቦታ አብርሃም ከኬጢያውያን#25፥10 ወይም የኬጢ ልጆች የገዛው ነበር፤ ከሚስቱ ከሣራ አጠገብ በዚያ ተቀበረ። 11አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ይሥሐቅን ባረከው፤ በዚህ ጊዜ ይሥሐቅ በብኤርላሃይሮኢ አቅራቢያ ይኖር ነበር።
የእስማኤል ልጆች
25፥12-16 ተጓ ምብ – 1ዜና 1፥29-31
12ግብጻዊቷ የሣራ አገልጋይ አጋር፣ ለአብርሃም የወለደችለት የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው።
13የእስማኤል ልጆች ስም እንደ ዕድሜያቸው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው፦
የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፣
ቄዳር፣ ነብዳኤል፣ መብሳም፣
14ማስማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣
15ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣
ናፌስና ቄድማ።
16እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው።
17እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 18ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብጽ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋራ በጠላትነት ኖሩ።#25፥18 ወይም በስተምሥራቅ ኖሩ
ያዕቆብና ዔሳው
19የአብርሃም ልጅ የይሥሐቅ ትውልድ ይህ ነው።
አብርሃም ይሥሐቅን ወለደ፤ 20ይሥሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች።
21ይሥሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች። 22ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሄደች።
23 እግዚአብሔርም እንዲህ አላት፤
“ሁለት ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤
ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤
አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤
ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” አላት።
24የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀኗ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ። 25በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጕር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው#25፥25 ዔሳው ማለት ጠጕራማ ማለት ነው፤ በተጨማሪ ኤዶም ተብሎ ተጠርቷል፤ ትርጕሙም ቀይ ማለት ነው። ተባለ። 26ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ#25፥26 ያዕቆብ ማለት ተረከዝ ይይዛል ማለት ነው፤ በምሳሌያዊ አገላለጽ ያታልላል ማለት ነው። ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይሥሐቅ የስድሳ ዓመት ሰው ነበር።
27ልጆቹም ዐደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር። 28ይሥሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወድደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድደው ነበር።
29አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ። 30ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ።
31ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው።
32ዔሳውም፣ “እነሆ፤ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ።
33ያዕቆብም ዔሳውን፣ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው፤ ስለዚህም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠለት።
34ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ።
ዔሳው ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት።
Currently Selected:
ዘፍጥረት 25: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.