እባብ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ “በርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሏልን?” አላት። ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።” እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከርሷም ጋራ ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ። የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ ዕራቍታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ። ስለዚህ የበለስ ቅጠል ሰፍተው አገለደሙ። ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሚስቱ ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው። አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው። አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋራ እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች። እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣ “ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤ “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል።” አዳምንም እንዲህ አለው፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣ “ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከርሷ ታገኛለህ። ምድርም እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች፤ ከቡቃያዋም ትበላለህ። ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት። እግዚአብሔር አምላክ ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው። ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ። ስለዚህ የተገኘበትን ምድር እንዲያርስ፣ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከዔድን የአትክልት ስፍራ አስወጣው፤ ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ ከዔድን በስተምሥራቅ አኖረ።
ዘፍጥረት 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 3
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 3:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos