ዘፍጥረት 35
35
ያዕቆብ ወደ ቤቴል ተመለሰ
1እግዚአብሔር ያዕቆብን፣ “ተነሥና ወደ ቤቴል ውጣ፤ እዚያም ተቀመጥ፤ ከወንድምህ ከዔሳው ሸሽተህ በሄድህ ጊዜ ለተገለጠልህ አምላክ በዚያ መሠዊያ ሥራ” አለው።
2ስለዚህም ያዕቆብ ለቤቱ ሰዎችና ዐብረውት ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ሰውነታችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ። 3ተነሥተን ወደ ቤቴል እንውጣ፤ እዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፣ በሄድሁበትም ስፍራ ሁሉ ላልተለየኝ አምላክ መሠዊያ እሠራለሁ።” 4ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ የነበሩትን ባዕዳን አማልክት ሰብስበው፣ የጆሮ ጕትቾቻቸውን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት። ያዕቆብም ወስዶ ሴኬም አጠገብ ካለው ወርካ ዛፍ ሥር ቀበራቸው። 5ያንም ቦታ ለቅቀው ሄዱ፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው በነበሩት ከተሞች ሁሉ ላይ ፍርሀትና ድንጋጤ ስለ ለቀቀባቸው የያዕቆብን ልጆች ያሳደዳቸው አልነበረም።
6ያዕቆብና ዐብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ፣ በከነዓን ወደምትገኘው፣ ቤቴል ወደተባለችው ወደ ሎዛ ደረሱ። 7ያዕቆብም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ ስሙን ኤል-ቤቴል#35፥7 ኤል-ቤቴል ማለት የቤቴል አምላክ ማለት ነው። አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ ሸሽቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር የተገለጠለት በዚህ ቦታ ነበር።
8በዚህ ጊዜ የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች፤ ከቤቴል ዝቅ ብሎ በሚገኘው ወርካ ዛፍ ሥር ተቀበረች። ከዚህ የተነሣም ያ ቦታ አሎንባኩት#35፥8 አሎንባኩት ማለት የልቅሶ ወርካ ማለት ነው። ተባለ።
9ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ እግዚአብሔር ለያዕቆብ ዳግመኛ ተገለጠለት፤ ባረከውም። 10እግዚአብሔርም፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ#35፥10 ያዕቆብ ማለት ተረከዝ ይይዛል ማለት ነው፤ በምሳሌያዊ አገላለጽ ያታልላል ማለት ነው። ነበረ፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል#35፥10 እስራኤል ማለት ከአምላክ ጋራ ታገለ ማለት ነው። ይባላል” አለው። ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው።
11ደግሞም እግዚአብሔር ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ቻይ#35፥11 በዕብራይስጥ ኤልሻዳይ ማለት ነው። አምላክ ነኝ፤ ብዛ ተባዛ፤ ሕዝብና የሕዝቦች ማኅበር ከአንተ ይወጣሉ፤ ነገሥታትም ከአብራክህ ይከፈላሉ። 12ለአብርሃምና ለይሥሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችኑ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።” 13እግዚአብሔርም ከርሱ ጋራ ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
14ያዕቆብም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ በተነጋገረበት ስፍራ የድንጋይ ሐውልት አቆመ፤ በሐውልቱ ላይ የመጠጥ ቍርባን አፈሰሰ፤ ዘይትም አፈሰሰበት። 15ያዕቆብም፣ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል#35፥15 ቤቴል ማለት የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው። ብሎ ጠራው።
የራሔልና የይሥሐቅ መሞት
35፥23-26 ተጓ ምብ – 1ዜና 2፥1-2
16ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፤ ምጡም ጠናባት። 17ምጡ አስጨንቋት ሳለ፣ አዋላጇ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገይ ነው” አለቻት። 18እርሷ ግን ሕይወቷ ልታልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች፣ ልጇን ቤንኦኒ#35፥18 ቤንኦኒ ማለት የመከራዬ ልጅ ማለት ነው። አለችው፤ አባቱ ግን ብንያም#35፥18 ብንያም ማለት የቀኜ ልጅ ማለት ነው። አለው።
19ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተ ልሔም ተቀበረች። 20ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከ ዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው።
21እስራኤልም ጕዞውን በመቀጠል ከጋዴር ወንዝ ባሻገር ድንኳኑን ተከለ። 22እስራኤልም በዚያ ምድር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋራ ተኛ፤ እስራኤልም ድርጊቱን ሰማ።
ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም፦
23የልያ ልጆች፦
የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል፣
ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤
24የራሔል ልጆች፦
ዮሴፍ፣ ብንያም፤
25የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦
ዳን፣ ንፍታሌም፤
26የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦
ጋድ፣ አሴር ናቸው።
እነዚህ ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ወንዶች ልጆች ነበሩ።
27ያዕቆብ አባቱ ወዳለበት ወደ መምሬ መጣ፤ አብርሃምና ይሥሐቅ የኖሩባት፣ ቂርያት አርባቅ ወይም ኬብሮን የተባለችው ቦታ ናት። 28ይሥሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤ 29ይሥሐቅም አርጅቶ፣ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።
Currently Selected:
ዘፍጥረት 35: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.