ዘፍጥረት 45

45
ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን ገለጠ
1በዚያ ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ፊት ስሜቱን ሊገታ ባለመቻሉ፣ “እዚህ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ስለዚህም ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት ጊዜ፣ ከርሱ ጋራ ሌላ ማንም ሰው አልነበረም። 2ዮሴፍም ድምፁን ከፍ አድርጎ በማልቀሱ፣ ግብጻውያን ሰሙት፤ ወሬውም ወደ ፈርዖን ቤተ ሰዎች ደረሰ።
3ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ ለመሆኑ አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” ሲል ጠየቃቸው። ወንድሞቹ ግን በፊቱ ተደናግጠው ስለ ነበር መልስ ሊሰጡት አልቻሉም።
4ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እስኪ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፤ ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ 5አሁንም በመሸጣችሁ አትቈጩ፤ በራሳችሁም አትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል። 6በምድር ላይ ራብ ከገባ ይኸው ሁለት ዓመት ሆነ፤ ከዚህ በኋላም የማይታረስባቸውና ሰብል የማይሰበሰብባቸው ዐምስት ዓመታት ገና አሉ። 7ነገር ግን እግዚአብሔር ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና#45፥7 ወይም በሕይወት እንደ ተረፉ ታላቅ ሰራዊት ለመታደግ ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ።
8“ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፣ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብጽ ምድር ላይ ገዥ አደረገኝ። 9አሁንም በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። 10ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ በጎችህን፣ ፍየሎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ። 11ገና ወደ ፊት የሚመጣ የዐምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ አለዚያ ግን አንተና ቤተ ሰዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’
12“ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዐይናችሁ የምታዩት ነው። 13በግብጽ ስላለኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ።”
14ከዚያም በወንድሙ በብንያም ዐንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን ዐቀፈው። 15የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከርሱ ጋራ መጨዋወት ጀመሩ።
16የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ ደስ አላቸው። 17ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንዲህ አድርጉ፤ አህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ። 18ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብጽ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሏችሁ ትኖራላችሁ።’
19“ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብጽ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጕዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ። 20ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፤ ከግብጽ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’ ”
21የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው። 22ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ጥሬ ብርና ዐምስት የክት ልብስ ሰጠው። 23ለአባቱም በግብጽ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም ለመንገዱ ስንቅ የሚሆነው እህል፣ ዳቦና ሌላ ምግብ በዐሥር እንስት አህዮች አስጭኖ ሰደደለት። 24ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከርሱም ሲሰናበቱ፣ “መንገድ ላይ እንዳትጣሉ!” አላቸው።
25እነርሱም ከግብጽ ወጥተው በከነዓን ምድር ወደሚኖረው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ መጡ። 26አባታቸውንም፣ “እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብጽ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኗል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብም በድንጋጤ ክው አለ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። 27ነገር ግን ዮሴፍ የነገራቸውን ሁሉ ሲያጫውቱትና እርሱንም ወደ ግብጽ ለማጓጓዝ ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። 28ከዚያም እስራኤል፤ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ልየው” አለ።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 45: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ