ዕብራውያን 8
8
የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት
1እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ 2እርሱም በሰው ሳይሆን በጌታ በተተከለችው፣ እውነተኛ ድንኳን በሆነችው ቤተ መቅደስ አገልጋይ ነው።
3እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት የሚሾመው መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ነው፤ ስለዚህ ይህኛውም ሊቀ ካህን የሚያቀርበው ነገር ያስፈልገዋል። 4እርሱ በምድር ቢኖር ኖሮ ካህን ባልሆነም ነበር፤ ምክንያቱም በሕግ በታዘዘው መሠረት መባን የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ። 5እነርሱ ያገለገሉት በሰማይ ላለችው መቅደስ ምሳሌና ጥላ በሆነችው ውስጥ ነው፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ለመሥራት በተነሣ ጊዜ፣ “በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት መሥራትህን ልብ በል”#8፥5 ዘፀ 25፥40 የሚል ትእዛዝ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ነበር። 6ነገር ግን ኢየሱስ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን ከቀድሞው እንደሚበልጥ ሁሉ፣ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፤ ይህም የተመሠረተው በተሻለ የተስፋ ቃል ላይ ነው።
7የመጀመሪያው ኪዳን ምንም ጕድለት ባይገኝበት ኖሮ፣ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። 8ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ጕድለት በማግኘቱ እንዲህ ይላቸዋል#8፥8 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ጕድለት በማግኘቱ ለሕዝቡ እንዲህ ይላቸዋል፤
“ከእስራኤል ቤትና፣
ከይሁዳ ቤት ጋራ፣
አዲስ ኪዳን የምገባበት፣
ጊዜ ይመጣል፤ ይላል ጌታ።
9ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣
እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣
ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤
ምክንያቱም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑም፤
እኔም ከእነርሱ ዘወር አልሁ፤
ይላል ጌታ።
10ከዚያ ጊዜ በኋላ፣
ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤
ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤
በልባቸውም እጽፈዋለሁ።
እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤
እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
11ከእንግዲህ ማንም ሰው ጎረቤቱን
ወይም ወንድሙን፣ ‘ጌታን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤
ምክንያቱም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ፣
ሁሉም ያውቁኛል።
12በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውን
ከእንግዲህ አላስብም።”#8፥12 ኤር 31፥31-34
13ይህን ኪዳን፣ “አዲስ” በማለቱ የፊተኛውን ኪዳን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ያረጀ ያፈጀው የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።
Currently Selected:
ዕብራውያን 8: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.