ሆሴዕ 14
14
በረከትን ለማግኘት ንስሓ መግባት
1እስራኤል ሆይ፤ በኀጢአትህ ምክንያት ስለ ወደቅህ፣
ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ።
2የምትሉትን ቃል ይዛችሁ፣
ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤
እንዲህም በሉት፤
“ኀጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤
የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ፣#14፥2 ወይም እንደ ኰርማዎች መሥዋዕት የከንፈራችንን ፍሬ እንድናቀርብ
በምሕረትህ ተቀበለን።
3አሦር ሊያድነን አይችልም፤
በጦር ፈረሶችም ላይ አንቀመጥም፤
ከእንግዲህም የገዛ እጆቻችን የሠሯቸውን፣
‘አምላኮቻችን’ አንላቸውም፤
ድኻ አደጉ ከአንተ ርኅራኄ ያገኛልና።”
4“እኔ ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ፤
እንዲሁ በፈቃደኛነት እወድዳቸዋለሁ፤
ቍጣዬ ከእነርሱ ተመልሷልና።
5እኔ ለእስራኤል እንደ ጠል እሆናለሁ፤
እንደ ውብ አበባ ያብባል፤
እንደ ሊባኖስ ዝግባም፣
ሥር ይሰድዳል፤
6ቅርንጫፉ ያድጋል፤
ውበቱ እንደ ወይራ ዛፍ፣
ሽታውም እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይሆናል።
7ሰዎች እንደ ገና ከጥላው በታች ያርፋሉ፤
እርሱም እንደ እህል ይለመልማል፤
እንደ ወይን ተክል ያብባል፤
ዝናውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ይወጣል።
8ኤፍሬም ሆይ፤ ከእንግዲህ ከጣዖት ጋራ ምን ጕዳይ አለኝ?#14፥8 ወይም ከእንግዲህ ከጣዖት ጋራ ኤፍሬም ሌላ ምን አለው?
የምሰማህና የምጠነቀቅልህ እኔ ነኝ፤
እኔ እንደ ለመለመ የጥድ ዛፍ ነኝ፤
ፍሬያማነትህም ከእኔ የተነሣ ነው።”
9ጥበበኛ የሆነ እነዚህን ነገሮች ያስተውላል፤
አስተዋይም እነዚህን ነገሮች ይረዳል።
የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነውና፤
ጻድቃን ይሄዱበታል፤
ዐመፀኞች ግን ይሰናከሉበታል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.