የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 10

10
1ፍትሕ የጐደለውን ሕግ ለሚያወጡ፣
ጭቈና የሞላበትን ሥርዐት ለሚደነግጉ ወዮላቸው!
2የድኾችን መብት ለሚገፍፉ፣
የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣
መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣
ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው!
3በምትጐበኙበት ቀን ምን ይውጣችኋል?
ጥፋት ከሩቅ ሲመጣስ ምን ትሆናላችሁ?
ርዳታን ለማግኘትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ?
ሀብታችሁንስ የት ታገኙታላችሁ?
4ከእስረኞች ጋራ ከመርበትበት፣
ከታረዱትም ጋራ ከመጣል በቀር ምንም አይተርፋችሁም።
በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው ገና አልበረደም፤
እጁም እንደ ተነሣ ነው።
የእግዚአብሔር ፍርድ በአሦር ላይ
5“የቍጣዬ በትር ለሆነ፣
የመቅሠፍቴም ዱላ በእጁ ላለው ለአሦራዊው ወዮለት!
6ሀብታቸውን እንዲዘርፍ፣ ምርኮን እንዲያግበሰብስ፣
እንደ መንገድ ላይ ጭቃም እንዲረግጣቸው፣
አምላክ በሌለው ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፣
በሚያስቈጣኝም ሕዝብ ላይ እሰድደዋለሁ።
7እርሱ ግን እንዲህ አላሰበም፤
በልቡም ይህ አልነበረም፤
ነገር ግን ዕቅዱ ለማጥፋት፣
ብዙ ሕዝቦችንም ለመደምሰስ ነበር።
8እንዲህም ይል ነበር፤
‘የጦር አዛዦቼ በሙሉ ነገሥታት አይደሉምን?’
9ካልኖ እንደ ከርከሚሽ፣
ሐማት እንደ አርፋድ፣
ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደሉምን?
10የጣዖታትን መንግሥታት፣
ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ መንግሥታት የሚበልጡትን እጄ እንደ ያዘች ሁሉ፣
11በሰማርያና በጣዖቶቿ ያደረግሁትን፣
በኢየሩሳሌምና በተቀረጹ ምስሎቿስ እንዲሁ አላደርግምን?”
12ጌታ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ የሚያደርገውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፣ እንዲህ ይላል፤ “የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ፤ 13የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፤
“ ‘ይህን ሁሉ ያደረግሁት በክንዴ ብርታት ነው፤
ደግሞም በጥበቤ አስተዋይ ነኝና።
የመንግሥታትን ድንበር አፈረስሁ፤
ሀብታቸውን ዘረፍሁ፤
ነገሥታታቸውን እንደ አንድ ኀያል ሆኜ አዋረድሁ።#10፥13 ወይም፣ ኀይላቸውን አዋረድሁ።
14ሰው እጁን ወደ ወፍ ጐጆ እንደሚሰድድ፣
እኔም እንዲሁ እጄን ወደ መንግሥታት ሀብት ሰደድሁ፤
ሰዎች የተተወ ዕንቍላል እንደሚሰበስቡ፣
እኔም እንዲሁ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤
ክንፉን ያራገበ የለም፤
አፉንም ከፍቶ የጮኸ አልነበረም።’ ”
15መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይኵራራልን?
መጋዝስ በሚስበው ላይ ይታበያልን?
በትር በሚያነሣው ሰው ላይ ራሱን እንደሚነቀንቅ፣
ዘንግም ራሱን ዕንጨት እንዳልሆነ አድርጎ እንደሚኵራራ ነው።
16ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
በፈረጠሙ ጦረኞቹ ላይ የሚያከሳ በሽታ ይልካል፤
ከክብሩም በታች እንደ ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳት
ይለኰሳል።
17የእስራኤል ብርሃን እሳት፣
ቅዱሱም ነበልባል ይሆናል፤
በአንድ ቀንም
እሾኹንና ኵርንችቱን እሳት ይበላዋል፤
18ሕመምተኛ እየመነመነ እንደሚሞት፣
የደኑን ክብርና የለማውን ዕርሻ፣
ነፍስና ሥጋንም ፈጽሞ ያጠፋል።
19በደኑ ውስጥ የሚተርፉት ዛፎች በጣም ጥቂት ናቸው፤
ሕፃን ልጅ እንኳ ቈጥሮ ሊመዘግባቸው ይችላል።
የተረፉት የእስራኤል ዘሮች
20በዚያ ቀን ከእስራኤል ዘር የተረፉት፣
ከያዕቆብም ቤት የዳኑት፣
ከእንግዲህ ወዲህ
በመታቸው ላይ አይታመኑም፤
ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ፣
በእውነት ይታመናሉ።
21የተረፉት ይመለሳሉ፣#10፥21 በዚህና በ22 ላይ ዕብራይስጡ፣ ሼር ጃሹብ ይላል (7፥3 እና በዚሁ ምዕራፍ ቍጥር 22ን ይመልከቱ)።
ከያዕቆብ ቤት የተረፉት ወደ ኀያሉ አምላክ ይመለሳሉ።
22እስራኤል ሆይ፤
ሕዝብህ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ቢሆንም፣
ትሩፉ ብቻ ይመለሳል።
ጽድቅ የሰፈነበት ጥፋት ታውጇል።
23የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
የወሰነውን ጥፋት በምድር ሁሉ ላይ ይፈጽማልና።
24ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
እንዲህ ይላል፤
“በጽዮን የምትኖሩ ሕዝቤ ሆይ፤
ግብጽ እንዳደረገብህ ሁሉ በትር ያነሡብህን፣
በሽመል የደበደቡህን አሦራውያንን አትፍራቸው።
25በአንተ ላይ ያመጣሁትን ቅጣት በጥቂት ጊዜ ውስጥ አቆማለሁ፤
በእነርሱም ላይ መቅሠፍቴን አመጣለሁ።”
26የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድያምን በሔሬብ ዐለት አካባቢ እንደ መታ፣
በጅራፍ ይገርፋቸዋል፤
በግብጽ እንዳደረገውም ሁሉ፣
በትሩን በውሆች ላይ ያነሣል።
27በዚያ ቀን ሸክማቸው ከትከሻህ፣
ቀንበራቸውም ከዐንገትህ ላይ ይነሣል፤
ከውፍረትህም የተነሣ
ቀንበሩ ይሰበራል።#10፥27 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን፣ ቀንበሩ ከትከሻህ ላይ ይሰበራል ይላል።
28ወደ ዐያት ይገባሉ፣
በሚግሮን ያልፋሉ፤
ጓዛቸውንም በማክማስ ያከማቻሉ።
29መተላለፊያውን ዐልፈው እንዲህ ይላሉ፤
“በጊብዓ ሰፍረን እናድራለን።”
ራማ ደነገጠች፤
የሳኦል ከተማ ጌባዕ ሸሸች።
30የጋሊም ሴት ልጅ ሆይ፤ ጩኺ!
ላይሻ ሆይ፤ አድምጪ!
ምስኪን ዓናቶት ሆይ፤ ስሚ!
31ማድሜናህ በሽሽት ላይ ናት፤
የጌቢም ሕዝብ ሊደበቅ ይሮጣል።
32በዚህ ቀን ኖብ ይደርሳሉ፤
እጃቸውን በኢየሩሳሌም ኰረብታ፣
በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ላይ
በዛቻ ነቀነቁ።
33እነሆ፤ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
በታላቅ ኀይል ቅርንጫፎችን ይቈራርጣል፤
ረዣዥም ዛፎች ይገነደሳሉ፤
ከፍ ከፍ ያሉትም ይወድቃሉ።
34ጥቅጥቅ ያለውን ደን በመጥረቢያ ይቈራርጣል፤
ሊባኖስም በኀያሉ ፊት ይወድቃል።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 10: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ