የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 41

41
የእስራኤል ረዳት
1“ደሴቶች ሆይ፤ በፊቴ ዝም በሉ፤
አሕዛብ ኀይላቸውን ያድሱ!
ቀርበው ይናገሩ፤
በፍርድም ፊት እንገናኝ።
2“ከምሥራቅ አንዱን ያነሣው፣
በጽድቅም ወደ አገልግሎቱ የጠራው ማን ነው?#41፥2 ወይም በእያንዳንዱ ርምጃ ድል የሚያጋጥመው
አሕዛብን አሳልፎ ሰጠው፤
ነገሥታትን በፊቱ አስገዛለት
በሰይፉም እንደ ትቢያ አቦነናቸው፤
በቀስቱም በነፋስ እንደ ተበተነ ገለባ አደረጋቸው።
3አሳደዳቸው፤ በሰላም ዐልፎ ሄደ፤
እግሩም ቀድሞ ባልረገጠው መንገድ ተጓዘ።
4ይህን የሠራና ያደረገ፣
ትውልድን ከጥንት የጠራ ማን ነው?
እኔ እግዚአብሔር ከፊተኛው፣
ከኋለኛውም ጋራ፤ እኔው ነኝ።”
5ደሴቶች አይተው ፈሩ፤
የምድር ዳርቾች ደነገጡ፤
ቀረቡ፤ ወደ ፊትም መጡ።
6እያንዳንዱ ይረዳዳል፤
ወንድሙንም፣ “አይዞህ!” ይለዋል።
7የእጅ ጥበብ ባለሙያው የወርቅ አንጥረኛውን ያበረታታዋል፤
በመዶሻ የሚያሳሳውም፣
በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያነቃቃዋል፤
ስለ ብየዳም ሥራው፣ “መልካም ነው” ይለዋል፤
የጣዖቱ ምስል እንዳይወድቅም በምስማር ያጣብቀዋል።
8“አንተ ግን፣ ባሪያዬ እስራኤል፣
የመረጥሁህ ያዕቆብ፣
የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፤
9ከምድር ዳርቻ ያመጣሁህ፣
ከአጥናፍም የጠራሁህ፣
‘አንተ ባሪያዬ ነህ’ ያልሁህ፤
መረጥሁህ እንጂ አልጣልሁህም።
10እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤
አምላክህ ነኝና አትደንግጥ።
አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤
በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።
11“እነሆ፤ የተቈጡህ ሁሉ፣
እጅግ ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም፤
የሚቋቋሙህ፣
እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም።
12ጠላቶችህን ብትፈልጋቸው እንኳ፣
አታገኛቸውም፤
የሚዋጉህም፣
እንዳልነበሩ ይሆናሉ።
13እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና አትፍራ ይልሃል፤
እረዳሃለሁ።
14አንተ ትል ያዕቆብ፣
ታናሽ እስራኤል ሆይ፤
‘አትፍራ እኔ እረዳሃለሁ’ ” ይላል እግዚአብሔር
የሚቤዥህ የእስራኤል ቅዱስ ነው።
15“እነሆ፣ አዲስ
የተሳለና ባለጥርስ ማሄጃ አደርግሃለሁ፤
ተራሮችን ታሄዳለህ፤ ታደቅቃቸዋለህ፤
ኰረብቶችንም ገለባ ታደርጋቸዋለህ።
16ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስ ጠርጎ ይወስዳቸዋል፤
ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል።
አንተ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤
በእስራኤል ቅዱስ ሞገስ ታገኛለህ።
17“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤
ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤
ጕረሯቸው በውሃ ጥም ደርቋል።
ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤
እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።
18በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣
በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮችን አፈልቃለሁ።
ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣
የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ።
19በምድረ በዳ፣
ዝግባን፣ ግራርን፣ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤
በበረሓ፣ ጥድን፣ አስታንና
ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ።
20ስለዚህ ሰዎች ያያሉ፤ ያውቃሉ፤
እግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣
የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠረው፣
በአንድነት ይገነዘባሉ፤ ያስተውላሉም።
21“ሙግታችሁን ይዛችሁ ቅረቡ” ይላል እግዚአብሔር
“ማስረጃችሁን አምጡ” ይላል የያዕቆብ ንጉሥ።
22“የሚሆነውን እንዲነግሩን፣
ጣዖቶቻችሁን አምጡ፤
እንድንገነዘብ፣
ፍጻሜአቸውን እንድናውቅ፣
የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ነበሩ ንገሩን፤
ስለሚመጡትም ነገሮች ግለጹልን።
23እናንተ አማልክት መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ፣
ወደ ፊት ስለሚሆነው ንገሩን፤
እንድንደነግጥ፣ በፍርሀት እንድንዋጥ፣
መልካምም ሆነ ክፉ፣ አንድ ነገር አድርጉ።
24እነሆ፤ እናንተ ከምንም የማትቈጠሩ ናችሁ፤
ሥራችሁ ፈጽሞ ዋጋ ቢስ ነው፤
የመረጣችሁም አስጸያፊ ነው።
25“አንዱን ከሰሜን አስነሣሁት፤ እርሱም ይመጣል፤
ከፀሓይ መውጫ የሚመጣው፣ ስሜን የሚጠራ ነው፤
ሸክላ ሠሪ ዐፈር እንደሚረግጥ፣
አለቆችን እንዲሁ እንደ ጭቃ ይረግጣል።
26እኛ እናውቅ ዘንድ ይህን ከመጀመሪያው የተናገረ፣
‘እርሱ ትክክል ነው’ እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረ ማነው?
ማንም አልተናገረም፤
ቀደም ብሎ የተናገረ የለም፤
ቃላችሁንም የሰማ የለም።
27በመጀመሪያ፣ ‘እነሆ፤ ተመልከቺአቸው!’
ብዬ ለጽዮን የተናገርሁ እኔ ነበርሁ፤
ለኢየሩሳሌምም
የምሥራች ነጋሪን ሰጥቻለሁ።
28ተመለከትሁ ማንም አልነበረም፤
ከመካከላቸው አማካሪ የለም፤
ስጠይቅም መልስ የሚሰጥ የለም።
29እነሆ፤ ሁሉም ከንቱ ናቸው!
ሥራቸውም መና ነው፤
ምስሎቻቸውም ባዶ ነፋስ ናቸው።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 41: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ