የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 42

42
እግዚአብሔር አገልጋይ
1“እነሆ፤ ደግፌ የያዝሁት፣
በርሱም ደስ የሚለኝ የመረጥሁት አገልጋዬ፤
መንፈሴን በርሱ ላይ አደርጋለሁ፤
ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል።
2አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤
ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም።
3የተቀጠቀጠ ሸንበቆ አይሰብርም፤
የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤
ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል።
4ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣
አይደክምም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤
ደሴቶች በሕጉ ይታመናሉ።”
5ሰማያትን የፈጠረ፣ የዘረጋቸውም፣
ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ፣
ለሕዝቧ እስትንፋስን፣
ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ፣
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
6“እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤
እጅህንም እይዛለሁ፤
እጠብቅሃለሁ፤
ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣
ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ።
7የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤
ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣
በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ።
8“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው!
ክብሬን ለሌላ፣
ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።
9እነሆ፤ የቀድሞው ነገር ተፈጽሟል፤
እኔም አዲስ ነገር እናገራለሁ፤
ከመብቀሉም በፊት፣
ለእናንተ አስታውቃለሁ።”
እግዚአብሔር የውዳሴ መዝሙር
10እናንተ ወደ ባሕር የምትወርዱ፣ በዚያም ያላችሁ ሁሉ፣
ደሴቶችና በዚያ የምትኖሩ በሙሉ፣
እግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣
ከምድር ዳርቻም ምስጋናውን ዘምሩ።
11ምድረ በዳውና ከተሞቹ ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤
ቄዳር ያለችበት መንደር ደስ ይበለው፤
የሴላ ሕዝቦች በደስታ ይዘምሩ፤
ከተራሮችም ራስ ላይ ይጩኹ።
12ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤
ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ።
13 እግዚአብሔር እንደ ኀያል ሰው ይዘምታል፤
እንደ ተዋጊ በቅናት ይነሣል፤
የቀረርቶ ጩኸት ያሰማል፤
ጠላቶቹንም ድል ያደርጋል።
14“ለረዥም ጊዜ ዝም አልሁ፤
ጸጥ አልሁ፤ ራሴንም ገታሁ፤
አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣
እጮኻለሁ፤ ቍና ቍና እቃትታለሁ፤ እተነፍሳለሁ።
15ተራራውንና ኰረብታውን አፈርሳለሁ፤
ዕፀዋቱን ሁሉ አደርቃለሁ፤
ወንዙንም ደሴት አደርጋለሁ፤
ኵሬውን አደርቃለሁ።
16ዕውሮችን በማያወቁት መንገድ
እመራቸዋለሁ፤
ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ።
ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤
ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ።
ይህን አደርጋለሁ፤
አልተዋቸውም።
17በጣዖት የሚታመኑ ግን፣
ምስሎችን፣ ‘አምላኮቻችን ናችሁ’ የሚሉ፣
ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ ፈጽመው ይዋረዳሉም።
ዕውሯና ደንቈሮዋ እስራኤል
18“እናንተ ደንቈሮዎች ስሙ፤
እናንተ ዕውሮች እዩ፤ ተመልከቱም!
19አገልጋዬ እንጂ፣ ሌላ ዕውር ማን አለ?
ከምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ማን ደንቈሮ አለ?
ለእኔ ታማኝ እንደ ሆነ ሰው የታወረ፣
እንደ እግዚአብሔርስ አገልጋይ ዕውር ማነው?
20ብዙ ነገርን አያችሁ፤ ነገር ግን አላስተዋላችሁም፤
ጆሯችሁ ክፍት ነው፤ ነገር ግን ምንም አትሰሙም።”
21 እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሲል፣
ሕጉን ታላቅና የተከበረ በማድረግ ደስ
አለው።
22ይህ ሕዝብ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ፣
በጕድጓድ ውስጥ የተጠመደበት፣
በወህኒ ቤት የተዘጋበት ነው፤
ተበዝብዘዋል፣
የሚያድናቸውም የለም፤
ተማርከዋል፣
“መልሷቸው” የሚልም የለም።
23ከእናንተ ይህን የሚሰማ፣
ለሚመጣውም ጊዜ አስተውሎ የሚያደምጥ ማነው?
24ያዕቆብን ለዝርፊያ፣
እስራኤልን ለምርኮ የዳረገ ማነው?
በኀጢአት የበደልነው፣
እግዚአብሔር አይደለምን?
መንገዱን ለመከተል፣
ለሕጉም መታዘዝ አልፈለጉምና።
25ስለዚህ የሚነድድ ቍጣውን፣
የጦርነትንም መዓት አፈሰሰባቸው፤
በእሳት ነበልባል ከበባቸው፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም፤
አቃጠላቸው፤ እነርሱ ግን ልብ አላሉም።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 42: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ