ኢሳይያስ 49
49
የእግዚአብሔር ባሪያ
1እናንተ ደሴቶች ስሙኝ፤
እናንተ በሩቅ ያላችሁ ሕዝቦች ይህን አድምጡ፤
በእናቴ ማሕፀን ሳለሁ እግዚአብሔር ጠራኝ፤
ከመወለዴ በፊት በስም ጠራኝ።
2አፌን እንደ ተሳለ ሰይፍ አደረገው፤
በእጁ ጥላ ሰወረኝ፤
የተወለወለ ፍላጻ አደረገኝ፤
በሰገባውም ውስጥ ሸሸገኝ።
3እርሱም፣ “እስራኤል፤ አንተ ባሪያዬ ነህ፤
በአንተ ክብሬን እገልጣለሁ” አለኝ።
4እኔ ግን፣ “ዐላማ ሳይኖረኝ እንዲሁ ደከምሁ፤
ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ነገር ጕልበቴን ጨረስሁ፤
ሆኖም ግን ብድራቴ በእግዚአብሔር እጅ፣
ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው” አልሁ።
5በእግዚአብሔር ዐይን ፊት ከብሬአለሁ፤
አምላኬ ጕልበት ሆኖልኛል፤
ባሪያው እንድሆን ከማሕፀን የሠራኝ፣
ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ፣
እስራኤልን ወደ እርሱ እንድሰበስብ ያደረገኝ፣
እግዚአብሔር አሁንም እንዲህ ይላል፤
6እርሱም፣
“ባሪያዬ መሆንህ፣
የያዕቆብን ነገዶች እንደ ገና መመለስህ፣
የጠበቅኋቸውን እስራኤል መልሰህ ማምጣት ለአንተ ቀላል ነገር ነው፤
ድነቴን እስከ ምድር ዳርቻ እንድታመጣ፣
ለአሕዛብ ብርሃን አደርግሃለሁ” አለኝ።
7 እግዚአብሔር፣
ታዳጊ የሆነው የእስራኤል ቅዱስ፣
ለተናቀውና በሕዝብ ለተጠላው፣
የገዦች አገልጋይ እንዲህ ይላል፤
“ነገሥታት አይተውህ ይነሣሉ፤
ልዑላንም አይተው ይሰግዳሉ፤
ምክንያቱም የመረጠህ የእስራኤል ቅዱስ፣
እግዚአብሔር ታማኝ ነው።”
የእስራኤል እንደ ገና መቋቋም
8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በተወደደ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤
በድነት ቀን እረዳሃለሁ።
ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣
ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣
ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣
እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤
9የተማረኩትን፣ ‘ኑ ውጡ’
በጨለማ ያሉትን፣ ‘ነጻ ሁኑ!’ እንድትል አድርጌሃለሁ።
“በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤
በተራቈተውም ኰረብታ ሁሉ ላይ መሰማሪያ ያገኛሉ።
10አይራቡም፤ አይጠሙም፤
የምድረ በዳ ትኵሳት ወይም የፀሓይ ቃጠሎ አይጐዳቸውም።
የሚራራላቸው ይመራቸዋል፤
በውሃ ምንጭ ዳርም ያሰማራቸዋል።
11ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤
ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ።
12እነሆ፤ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤
አንዳንዶች ከሰሜን ሌሎች ከምዕራብ፣
የቀሩት ደግሞ ከሲኒም#49፥12 የማሶሬቱ ቅጅ ከዚህ ጋራ ይስማማል፣ የሙት ባሕር ጥቅልሎች ግን፣ አስዋን ይላሉ። ይመጣሉ።”
13ሰማያት ሆይ፤ እልል በሉ፤
ምድር ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤
ተራሮች ሆይ፤ በደስታ ዘምሩ!
እግዚአብሔር ሕዝቡን ያጽናናል፤
ለተቸገሩትም ይራራልና።
14ጽዮን ግን፣ “እግዚአብሔር ትቶኛል፤
ጌታም ረስቶኛል” አለች።
15“እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን?
ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን?
ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣
እኔ ግን አልረሳሽም!
16እነሆ፤ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤
ቅጥሮችሽ ምን ጊዜም በፊቴ ናቸው።
17ወንዶች ልጆችሽ ፈጥነው ይመለሳሉ፤
ያፈራረሱሽም ከአንቺ ይሸሻሉ።
18ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤
ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ።
እኔ ሕያው ነኝ፤
እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤
እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር።
19“ፈራርሰሽ ባድማ ብትሆኚ፣
ምድርሽ ፈጽሞ ቢጠፋ፣
ዛሬ ለሕዝብሽ ጠባብ ብትሆኚም እንኳ፣
የዋጡሽ ከአንቺ ይርቃሉ።
20በሐዘንሽ ዘመን የወለድሻቸው ልጆች፣
ጆሮሽ እየሰማ፣
‘ይህ ቦታ በጣም ጠብቦናል፤
የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይሉሻል።
21በልብሽም እንዲህ ትያለሽ፣
‘እነዚህን የወለደልኝ ማን ነው?
እኔ ሐዘንተኛና መካን፣
የተሰደድሁና የተጠላሁ ነበርሁ፤
እነዚህን ማን አሳደጋቸው?
ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤
ታዲያ፣ እነዚህ ከየት መጡ?’ ”
22ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ አሕዛብን በጥቅሻ እጣራለሁ፤
ዐርማዬንም ለሕዝቦች ከፍ አደርጋለሁ፤
ወንዶች ልጆችሽን በዕቅፋቸው ያመጡልሻል፤
ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ይሸከሙልሻል።
23ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ፣
እቴጌዎቻቸው ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤
በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤
የእግርሽን ትቢያ ይልሳሉ፤
አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤
እኔን ተስፋ የሚያደርጉም አያፍሩም።”
24ከተዋጊ ብዝበዛ ማስጣል፣
ከጨካኝስ#49፥24 የሙት ባሕር ጥቅልሎች፣ ቩልጌትና የሱርስቱ ቅጅ (እንዲሁም የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም 25 ይመ) ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ ከጻድቅስ ይላል። ምርኮኞችን ማዳን ይቻላልን?
25 እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤
“ከተዋጊዎች ላይ ምርኮኞች በርግጥ ይወሰዳሉ፤
ከጨካኞችም ላይ ምርኮ ይበዘበዛል፤
ከአንቺ ጋራ የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፤
ልጆችሽንም እታደጋለሁ።
26አስጨናቂዎችሽ የራሳቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤
በወይን ጠጅ እንደሚሰከር ሁሉ፣ በገዛ ደማቸው ይሰክራሉ።
ከዚያም የሰው ዘር ሁሉ፣
እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣
ታዳጊሽም የያዕቆብ ኀያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።”
Currently Selected:
ኢሳይያስ 49: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.