የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 52

52
1ጽዮን ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤
ኀይልን ልበሺ፤
ቅድስቲቱ ከተማ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ!
የክብር ልብስሽን ልበሺ፤
ያልተገረዘ የረከሰም
ከእንግዲህ ወደ አንቺ አይገባም።
2ትቢያሽን አራግፊ፤
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ በዙፋንሽ ላይ ተቀመጪ፤
ምርኮኛዪቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፤
የዐንገትሽን የእስራት ሰንሰለት አውልቀሽ ጣዪ።
3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ያለ ዋጋ ተሸጣችሁ ነበር፤
ያለ ገንዘብ ትቤዣላችሁ።”
4ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በመጀመሪያ ሕዝቤ ይኖር ዘንድ ወደ ግብጽ ወረደ፤
በኋላም አሦር ያለ ምክንያት አስጨንቆ ገዛው።
5“አሁን እዚህ ምን አለኝ?” ይላል እግዚአብሔር
“ሕዝቤ ያለ ምክንያት ተወስዷል፤
የገዟቸው ተሣልቀውባቸዋል”#52፥5 የሙት ባሕር ጥቅልሎችና ቩልጌት ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ ሙሾ ይላል።
ይላል እግዚአብሔር
“ቀኑን ሙሉ፣
ስሜ ያለ ማቋረጥ ይሰደባል።
6ስለዚህ ሕዝቤ ስሜን ያውቃል፤
በዚያ ቀንም፣
አስቀድሜ የተናገርሁ እኔ መሆኔን ይረዳል፤
እነሆ፤ እኔው ነኝ።”
7በተራሮች ላይ የቆሙ፣
የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች፣
ሰላምን የሚናገሩ፣
መልካም ዜና የሚያበሥሩ፣
ድነትን የሚያውጁ፣
ጽዮንንም፣
“አምላክሽ ነግሧል!” የሚሉ እንዴት ያማሩ ናቸው።
8ስሚ! ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገዋል፤
በአንድነት በእልልታ ይዘምራሉ።
እግዚአብሔር ወደ ጽዮን ሲመለስ፣
በዐይኖቻቸው ያያሉ።
9እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች፣
በአንድነት በእልልታ ዘምሩ፤
እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቷል፤
ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቷልና።
10 እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣
የተቀደሰ ክንዱን ይገልጣል፤
በምድር ዳርቻዎች ያሉ ሁሉ፣
የአምላካችንን ማዳን ያያሉ።
11እናንተ የእግዚአብሔርን ዕቃ የምትሸከሙ፣
ተለዩ! ተለዩ! ከመካከልዋ ውጡ፤
ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤
ከዚያ ውጡ ንጹሓንም ሁኑ፤
12ሆኖም በችኰላ አትወጡም፤
ሸሽታችሁም አትሄዱም፤
እግዚአብሔር ፊት ፊታችሁ ይሄዳል፤
የእስራኤል አምላክ ደጀን ይሆናችኋል።
የባሪያው ሥቃይና ክብር
13እነሆ፤ ባሪያዬ የሚያከናውነው በማስተዋል ነው፤#52፥13 ወይም ባሪያዬ ይበለጽጋል
ገናና ይሆናል፤ ከፍ ከፍ ይላል፤ እጅግ ይከብራልም።
14ብዙዎች በርሱ#52፥14 ዕብራይስጡ፣ በአንተ ይላል። እስኪደነግጡ ድረስ፣
መልኩ ከማንም ሰው ተለየ፤
ከሰው ልጆችም ሁሉ ይልቅ ተጐሳቈለ።
15ስለዚህ ብዙ መንግሥታትን ያስደንቃል፤
በርሱ ምክንያት ነገሥታት አፋቸውን ይይዛሉ፤
ያልተነገራቸውን ያያሉ፤
ያልሰሙትንም ያስተውላሉ።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 52: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ