ኢሳይያስ 62
62
አዲሱ የጽዮን ስም
1ጽድቋ እንደ ማለዳ ወጋገን እስኪፈነጥቅ፣
ድነቷ እንደሚያንጸባርቅ ፋና እስኪታይ፣
ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤
ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም።
2መንግሥታት ጽድቅሽን፣
ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤
የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣
በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።
3በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፣
በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።
4ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤
ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤
ነገር ግን፣ “ደስታዬ በርሷ” ትባያለሽ፤
ምድርሽም፣ “ባለባል” ትባላለች፤
እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤
ምድርሽም ባለባል ትሆናለች።
5ጕልማሳ ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣
ልጆችሽ#62፥5 ወይም፣ ግንበኞችሽ እንዲሁ ያገቡሻል፤
ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣
አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል።
6ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤
ቀንም ሆነ ሌሊት ፈጽሞ አይታክቱም።
እናንተ ወደ እግዚአብሔር አቤት፣ አቤት የምትሉ፤
ፈጽሞ አትረፉ፤
7ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት፣
የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ዕረፍት አትስጡት።
8 እግዚአብሔር በቀኝ እጁ፣
በኀያል ክንዱም እንዲህ ሲል ምሏል፤
“ከእንግዲህ እህልሽን፣
ለጠላቶችሽ መብል እንዲሆን አልሰጥም፤
ከእንግዲህ የደከምሽበትን፣
አዲስ የወይን ጠጅ ባዕዳን አይጠጡትም።
9ነገር ግን መከሩን የሰበሰቡ ይበሉታል፤
እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፤
የወይኑን ፍሬ የለቀሙም በመቅደሴ
አደባባዮች ይጠጡታል።”
10ዕለፉ፤ በበሮቹ በኩል ዕለፉ፤
ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ፤
አስተካክሉ፤ ጐዳናውን አስተካክሉ!
ድንጋዩን አስወግዱ፤
ለመንግሥታትም ምልክት አሳዩ።
11 እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ፣
እንዲህ ሲል ዐውጇል፤
“ለጽዮን ሴት ልጅ፣
‘እነሆ፤ አዳኝሽ መጥቷል!
ዋጋሽ በእጁ አለ፤
ዕድል ፈንታሽም ከርሱ ጋራ ነው’ በሏት።”
12እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣
እግዚአብሔር የተቤዣቸው ተብለው ይጠራሉ፤
አንቺም የምትፈለግ፣
ከእንግዲህም የማትተው ከተማ ትባያለሽ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.