ኢሳይያስ 7
7
የዐማኑኤል ምልክትነት
1የዖዝያን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፣ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም።
2ለዳዊት ቤት፣ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል#7፥2 ወይም ዘምተዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ።
3 እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “አንተና ልጅህ ሸአር ያሹብ#7፥3 ሸአር ያሹብ ማለት፣ ቅሬታዎች ይመለሳሉ ማለት ነው። አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤ 4እንዲህም በለው፤ ‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ፤ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጕማጆች፣ በሶርያና በንጉሥዋ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቍጣ አትሸበር። 5ሶርያ ኤፍሬምና፣ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ 6“ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው፤ ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባት።” 7ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤
“ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤
ከቶም አይደረግም፤
8የሶርያ ራስ ደማስቆ፣
የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤
በስድሳ ዐምስት ዓመት ውስጥ፣
የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል።
9የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፣
የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው።
እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፣
ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ ”
10እንደ ገናም እግዚአብሔር አካዝን እንዲህ አለው፤ 11“ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ለምን።”
12አካዝ ግን፣ “አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ።
13ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ! የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? 14ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል#7፥14 ወይም ወጣት ሴት ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል#7፥14 ዐማኑኤል ማለት፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ማለት ነው። ትለዋለች። 15ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። 16ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። 17ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።”
18በዚያ ቀን እግዚአብሔር ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። 19እነርሱም በሙሉ መጥተው፣ በየበረሓው ሸለቆ፣ በየዐለቱ ንቃቃት፣ በየእሾኹ ቍጥቋጦና በየውሃው ጕድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። 20በዚያ ቀን፣ እግዚአብሔር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፣ ማለትም በአሦር ንጉሥ፣ የራስና የእግር ጠጕራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። 21በዚያ ቀን፣ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። 22ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። 23በዚያ ቀን ሺሕ ሰቅል#7፥23 12 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር የሚያወጣ አንድ ሺሕ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፣ ኵርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። 24ምድሪቱ በኵርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፣ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ 25ኵርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደ ነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብቶች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.