መሳፍንት 15
15
ሳምሶን ፍልስጥኤማውያንን ተበቀለ
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ለማየት ሄደ፤ እርሱም፣ “ሚስቴ ወዳለችበት ጫጕላው ቤት ልግባ” አለ፤ አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም።
2አባትየውም፣ “ፈጽሞ የጠላሃት መሆንህን ስለ ተረዳሁ ለሚዜህ ድሬለታለሁ፤ ታናሽ እኅቷ ከርሷ ይልቅ ውብ አይደለችምን? እርሷን አግባት” አለው።
3ሳምሶንም መልሶ፣ “ከእንግዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ በሚደርሰው ጕዳት ተጠያቂ አልሆንም” አላቸው። 4ከዚያም ወጥቶ በመሄድ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ የሁለት ሁለቱን ጭራ አንድ ላይ ካሰረ በኋላ ችቦ ወስዶ ጥንድ ሆኖ ከተያያዘው ጭራ ጋራ አሰረው። 5ችቦውን በእሳት አቀጣጥሎ ቀበሮቹን በፍልስጥኤማውያን የእህል አዝመራ ላይ ለቀቃቸው፤ ነዶውንና የቆመውን አዝመራ እንዲሁም የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠለ።
6ፍልስጥኤማውያን፣ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ፣ “ሚስቱ ለሚዜው ስለ ተሰጠችበት የተምናዊው ዐማች ሳምሶን ነው” የሚል መልስ አገኙ።
ስለዚህም ፍልስጥኤማውያን ወጥተው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጥለው ገደሏቸው። 7ሳምሶንም፣ “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ ሳልበቀላችሁ አልመለስም” አለ። 8ክፉኛ መታቸው፤ ከእነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኤጣም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ።
9ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ። 10የይሁዳም ሰዎች፣ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው።
እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ልናስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው።
11ከዚያም ሦስት ሺሕ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤጣም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፣ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
ሳምሶንም፣ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው።
12እነርሱም፣ “አስረን ለፍልስጥኤማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት።
ሳምሶንም፣ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።
13እነርሱም፣ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት። 14ሳምሶን ሌሒ እንደ ደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ። 15ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺሕ ሰው ገደለ።
16ሳምሶንም፣
“በአንድ የአህያ መንጋጋ፣
ሺሕ ሰው ዘራሪ፤
በአንድ የአህያ መንጋጋ፣
ሺሕ ሬሳ አነባባሪ#15፥16 በዕብራይስጡ አህያ የሚለው ቃል ፍም ከመረ ወይም አነባበረ ከሚለው ጋራ ተመሳሳይ ነው።” ብሎ ፎከረ።
17ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የአህያውን መንጋጋ ከእጁ ወዲያ ወረወረው፤ የዚያም ቦታ ስም ራማት ሌሒ#15፥17 ራማት ሌሒ ማለት የመንጋጋ ኰረብታ ክምር ማለት ነው። ተብሎ ተጠራ።
18እጅግ ተጠምቶ ስለ ነበር፤ “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ?” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 19እግዚአብሔርም በሌሒ ዐለት ሰነጠቀለት፤ ከዚያም ውሃ ወጣ፤ ሳምሶንም ያን ሲጠጣ በረታ፤ መንፈሱም ታደሰ። ስለዚህ ያ ምንጭ ዓይንሀቆሬ#15፥19 ዓይንሀቆሬ ማለት የጠሪዎች ምንጭ ማለት ነው ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው በሌሒ ይገኛል።
20ሳምሶንም በፍልስጥኤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሃያ ዓመት ፈራጅ#15፥20 በትውፊት መሳፍንት ይባላል። ሆነ።
Currently Selected:
መሳፍንት 15: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.