የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 9

9
አቤሜሌክ
1የይሩባኣል ልጅ አቢሜሌክ ወደ እናቱ ወንድሞች ወደ ሴኬም ሄደ። እነርሱንና የእናቱን ጐሣዎች በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ 2“የሴኬምን ነዋሪዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፤ ‘ሰባዎቹ የይሩባኣል ልጆች ቢገዟችሁ ይሻላል ወይስ አንድ ሰው ብቻ?’ የሥጋችሁ ቍራጭ፣ የዐጥንታችሁ ፍላጭ መሆኔን ልብ በሉ።”
3የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ገዦች በሙሉ ነገሩ፤ አቢሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ዳዳ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል” ብለዋልና። 4እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል#9፥4 0.8 ኪሎ ግራም ያህል ነው ብር ሰጡት፤ አቢሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት። 5ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩባኣልን ልጆች፣ ወንድሞቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩባኣል የመጨረሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ። 6የሴኬምና የቤት ሚሎ ገዦች በሙሉ አቢሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ።
7ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ “የሴኬም ገዦች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ። 8ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
9“የወይራ ዛፍም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?’ አለ።
10“ቀጥሎም ዛፎቹ በለስን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
11“በለስ ግን፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እጅግ ጣፋጭና መልካም የሆነውን ፍሬዬን መስጠት ልተውን?’ አለ።
12“ከዚያም ዛፎቹ የወይን ተክልን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
13“የወይን ተክሉም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ አማልክትንና ሰዎችን ደስ የሚያሠኘውን የወይን ጠጄን መስጠት ልተውን?’ አለ።
14“በመጨረሻም ዛፎቹ በሙሉ የእሾኽ ቍጥቋጦን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
15“የእሾኽ ቍጥቋጦውም ዛፎቹን፣ ‘በርግጥ ቀብታችሁ በላያችሁ የምታነግሡኝ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ግን እሳት ከእሾኽ ቍጥቋጦው ይነሣ፤ የሊባኖስንም ዝግባዎች ይብላ!’ አላቸው።
16“እንግዲህ አቢሜሌክን ስታነግሡት በእውነትና ያለ እንከን አድርጋችሁት ከሆነ፣ ይሩባኣልንና ቤተ ሰቡን በበጎ ዐይን ተመልክታችሁ ላደረገው የሚገባውን አይታችሁለት ከሆነ፣ 17አባቴ ለእናንተ መዋጋቱን፣ ከምድያማውያን እጅ ሊያድናችሁ ሕይወቱን መስጠቱን ዐሰባችሁ ማለት ነው። 18ነገር ግን እናንተ ዛሬ በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ዐመፃችሁ፤ ሰባ ልጆቹን በአንዲት ድንጋይ ላይ ዐረዳችሁ፤ ዘመዳችሁ ስለ ሆነም አባቴ ከባሪያው የወለደውን ልጅ አቢሜሌክን በሴኬም ገዦች ላይ አነገሣችሁት። 19እንግዲህ ዛሬ በይሩባኣልና በቤተ ሰቡ ላይ ያደረጋችሁት በእውነትና ያለ እንከን ከሆነ እናንተ በአቢሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም በእናንተ ደስ ይበለው! 20ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቢሜሌክ ትውጣና እናንተን፣ የሴኬምንና የቤት ሚሎን ነዋሪዎች ትብላ፤ እንዲሁም እሳት ከእናንተ፣ ከሴኬምና ከቤት ሚሎን ገዦች ትውጣና አቢሜሌክን ትብላ።”
21ከዚህ በኋላ ኢዮአታም ሸሽቶ አመለጠ፤ ብኤር ወደ ተባለች ቦታም መጣ፤ ወንድሙንም አቢሜሌክን ፈርቶ ስለ ነበር እዚያው ይኖር ጀመር።
22አቢሜሌክ እስራኤልን ሦስት ዓመት ከገዛ በኋላ፣ 23እግዚአብሔር በአቢሜሌክና በሴኬም ገዦች መካከል ክፉ መንፈስ ሰደደ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች አቢሜሌክን ከዱት። 24ይህን ያደረገውም፣ በሰባው የይሩባኣል ልጆች ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍና ስለ ፈሰሰው ደማቸው፣ ወንድማቸውን አቢሜሌክና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬም ገዦች ለመበቀል ነው። 25የሴኬም ገዦችም አቢሜሌክን ሸምቀው የሚጠባበቁትን ሰዎች መደቡ፤ ሰዎቹም እርሱን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በዚያ የሚያልፈውን ሁሉ ዘረፉ፤ ወሬውም ለአቢሜሌክ ደረሰው።
26በዚህ ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋራ ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ገዦች ተማመኑበት። 27ወደ ዕርሻ ወጥተው ወይናቸውን ለቅመው ከጨመቁ በኋላ በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ አቢሜሌክን ሰደቡ። 28የአቤድ ልጅ ገዓል እንዲህ አለ፤ “እንገዛለት ዘንድ አቢሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድን ናት? እርሱ የይሩባኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የርሱ ረዳት ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤ ለምን ለአቢሜሌክ እንገዛለን? 29ምነው ይህን ሕዝብ የማዝዘው እኔ በሆንሁ ኖሮ! አቢሜሌክን አስወግደው ነበር፤ ‘ሰራዊትህን አብዝተህ ውጣ#9፥29 ዕብራይስጡ አቤሜሌክን እንዲህ አለው፤ ሰራዊትህን ሁሉ ጥራ! ይላል።!’ እለው ነበር።”
30የከተማዪቱ ገዥ ዜቡል፣ የአቤድ ልጅ ገዓል ያለውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ 31ወደ አቢሜሌክም መልእክተኞች በምስጢር ልኮ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተው ከተማዪቱ እንድትሸፍትብህ አድርገዋል። 32ስለዚህ በሌሊት ሰዎችህን ይዘህ ወጥተህ ሜዳው ላይ ማድፈጥ አለብህ፤ 33ጧት ፀሓይ ስትወጣም ወደ ከተማዪቱ ገሥግሥ፤ ገዓልና ሰዎቹ ሊገጥሙህ በሚወጡበት ጊዜ እጅህ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርግ።”
34ስለዚህ አቢሜሌክና ሰዎቹ በሙሉ በሌሊት ወጡ፤ በአራት ምድብ ሆነውም በሴኬም አጠገብ አደፈጡ። 35የአቤድ ልጅ ገዓል ከከተማዪቱ ወጥቶ በመግቢያው በር ላይ ሲቆም፣ አቢሜሌክና ሰዎቹ ካደፈጡበት ወጡ።
36ገዓል ባያቸው ጊዜ ዜቡልን፣ “ተመልከት፤ ከተራራው ጫፍ ሕዝብ እየወረደ ነው” አለው።
ዜቡልም መልሶ፣ “የተራሮች ጥላ ሰዎች መስሎ ተሳስተህ” ነው አለው።
37ገዓልም፣ “ተመልከት እንጂ ሕዝብ እኮ ከተራራው ወገብ ላይ እየደረሰ ነው፤ አንዱ ክፍልም በቃላተኞች ዛፍ በኩል አድርጎ እየመጣ ነው” ብሎ እንደ ገና ተናገረ።
38ከዚያም ዜቡል፣ “እንገዛለት ዘንድ አቢሜሌክ ማን ነው? ብለህ የደነፋኸው አሁን የት አለ? ያቃለልሀቸውስ ሰዎች እነዚህ አይደሉምን? በል ውጣና ግጠማቸው” አለው።
39ገዓል የሴኬምን ገዦች መርቶ በመውጣት አቢሜሌክን ተዋጋው፤ 40ሆኖም አቢሜሌክ አሳደደው፤ እስከ መግቢያው በር ድረስ ባለው መንገድ ሲሸሹም ብዙ ሰዎች ቈስለው ወደቁ። 41አቢሜሌክ በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው።
42በማግስቱም የሴኬም ሕዝብ ወደ ዕርሻ ወጡ፤ ይህም ለአቢሜሌክ ተነገረው፤ 43እርሱም ሰዎቹን አስከትሎ ወጣ፤ ከዚያም ሰዎቹን ሦስት ቦታ መድቦ በዕርሻዎቹ ውስጥ አድፍጠው እንዲጠባበቁ አደረገ። አቢሜሌክ የሴኬም ሰዎች ከከተማዪቱ መውጣታቸውን እንዳየም ካደፈጠበት ሊወጋቸው ተነሣ። 44ከዚያም አቢሜሌክና ዐብረውት የነበሩ ምድቦች ቦታ ለመያዝ በፍጥነት ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በሚሮጡበት ጊዜ፣ ሌሎቹ ሁለት ምድቦች ደግሞ እየሮጡ ሄደው በዕርሻው ያሉትን ሁሉ ፈጇቸው። 45በዚያ ዕለት አቢሜሌክ ቀኑን ሙሉ ከተማዪቱን ሲወጋ ውሎ በመጨረሻ ያዛት፤ ሕዝቧን ፈጀ፤ ከተማዪቱንም አጠፋ፤ በላይዋም ጨው ዘራባት።
46በሴኬም ግንብ ውስጥ የሚኖሩ ገዦች ይህን እንደ ሰሙ፤ በኤልበሪት ቤተ መቅደስ ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገቡ። 47አቢሜሌክም በሴኬም ግንብ ገዦች ሁሉ መመሸጋቸውን ሲሰማ፣ 48እርሱና ሰዎቹ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቢሜሌክም መጥረቢያ ወስዶ ጥቂት የዛፍ ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ በትከሻውም ላይ አደረገ። የተከተሉትንም ሰዎች፣ “ፍጠኑ፤ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን አድርጉ” ሲል አዘዛቸው። 49ሰዎቹም ሁሉ ቅርንጫፎች ቈርጠው አቢሜሌክን ተከተሉት፤ ቅርንጫፎቹንም ምሽጉ ላይ አስደግፈው በመከመር ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ በእሳት አቃጠሏቸው። ስለዚህ በሴኬም ግንብ ውስጥ የነበሩት አንድ ሺሕ ያህል ወንዶችና ሴቶች ሞቱ።
50ከዚያም አቢሜሌክ ወደ ቴቤስ በመሄድ ከተማዪቱን ከብቦ ያዛት። 51ሆኖም በከተማዪቱ ውስጥ ብርቱ ግንብ ስለ ነበር፣ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ የከተማዪቱ ገዦችም ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በውስጥ ዘግተው ወደ ግንቡ ጣራ ወጡ። 52አቢሜሌክም ተዋግቶ ግንቡን ያዘ፤ ይሁን እንጂ እሳት ለመለኰስ ወደ ግንቡ መግቢያ አጠገብ እንደ ደረሰ፣ 53አንዲት ሴት ከላይ የወፍጮ መጅ በአቢሜሌክ ራስ ላይ ለቀቀችበት፤ ጭንቅላቱንም አፈረሰችው።
54ወዲያውም ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ፣ “ ‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉ እባክህ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ” አለው። ስለዚህ አገልጋዩ ወጋው፤ እርሱም ሞተ። 55እስራኤላውያንም አቢሜሌክ መሞቱን ሲያዩ ወደ የቤታቸው ተመለሱ።
56አቢሜሌክ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል፣ በአባቱ ላይ ስላደረሰው በደል እግዚአብሔር የእጁን ከፈለው። 57በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰው፤ የይሩባኣል ልጅ የኢዮአታም ርግማን ደረሰባቸው።

Currently Selected:

መሳፍንት 9: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ