ዮናስ 4
4
ዮናስ እግዚአብሔር ምሕረት በማድረጉ ተቈጣ
1ዮናስ ግን ፈጽሞ አልተደሰተም፤ ስለዚህም ተቈጣ። 2ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁትስ ይህን አልነበረምን? ፈጥኜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የተነሣሁትም ለዚሁ ነበር፤ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣ የዘገየህ አምላክ፣ ምሕረትህ የበዛ፣ ጥፋትንም ከማምጣት የምትመለስ እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ። 3አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ውሰድ፤ ከመኖር መሞት ይሻለኛልና።”
4 እግዚአብሔር ግን፣ “በውኑ ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው።
5ዮናስም ከከተማዪቱ ወጥቶ በስተምሥራቅ በአንድ ስፍራ ተቀመጠ። በዚያም ለራሱ ዳስ ሠራ፤ በከተማዪቱም የሚሆነውን ለማየት ከዳሱ ጥላ ሥር ተቀመጠ። 6እግዚአብሔር አምላክም የቅል ተክል#4፥6 የዚህ ተክል ትክክለኛ ስም ግልጥ አይደለም። በተጨማሪም በቍጥር 7፣ በ9 እና በ10 አለ። አብቅሎ፣ የዮናስ ራስ ጥላ እንዲያገኝና ሙቀትም እንዳያስጨንቀው ከበላዩ እንዲያድግ አደረገ፣ ዮናስም ስለ ቅሉ እጅግ ደስ አለው። 7ነገር ግን በሚቀጥለው ቀን በማለዳ እግዚአብሔር ትል አመጣ፤ ትሉም ቅሉን በላ፤ ቅሉም ደረቀ። 8ፀሓይ ስትወጣ፣ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አመጣ፤ ፀሓዩም የዮናስን ራስ አቃጠለ፤ እርሱም ተዝለፈለፈ፤ መሞትም ፈልጎ፣ “ከመኖር መሞት ይሻለኛል” አለ።
9እግዚአብሔር ግን ዮናስን፣ “በውኑ ስለ ቅሉ ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው።
እርሱም፣ “በርግጥ እስከ ሞት ልቈጣ ይገባኛል” አለ።
10 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለው፤ “አንተ እንዲበቅል ወይም እንዲያድግ ላልደከምህበት ለዚህ ቅል እጅግ ዐዝነሃል፤ በአንድ ሌሊት በቀለ፤ በአንድ ሌሊትም ደረቀ። 11ታዲያ፣ እኔ ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሳት ለሚኖሩባት ለታላቋ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.