ኢያሱ 10
10
ፀሓይ ቆመች
1የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን ይዞ እንደ ደመሰሳት#10፥1 የዕብራይስጡ ቃል በዚህም ሆነ በቍጥር 28፣ 35፣ 37፣ 39 እና 40 ላይ ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው።፣ እንደዚሁም በኢያሪኮና በንጉሧ ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በጋይና በንጉሧ ላይ ማድረጉን፣ የገባዖን ሰዎችም ከእስራኤል ጋራ የሰላም ውል አድርገው በአጠገባቸው መኖራቸውን ሰማ። 2በዚህም እርሱና ሕዝቡ ደነገጡ፤ ምክንያቱም ገባዖን እንደ ነገሥታቱ ከተማ ሁሉ ታላቅ ከተማ፣ በስፋቷም ከጋይ የምትበልጥ፣ ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ። 3ስለዚህ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ሆሃም ወደተባለው የኬብሮን ንጉሥ ጲርአም ወደተባለው የያርሙት ንጉሥ፣ ያፊዓ ወደተባለው የለኪሶ ንጉሥና ዳቤር ወደተባለው የዔግሎን ንጉሥ በመላክ፣ 4“ወደዚህ ወጥታችሁ አግዙኝ፤ ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋራ ሰላምን መሥርታለችና ገባዖንን እንምታ” አላቸው።
5ከዚያም ዐምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለት የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የዔግሎን ንጉሥ ያላቸውን አስተባብረው፣ ሰራዊታቸውንም ሁሉ ይዘው በመውጣት ገባዖንን ወጓት።
6የገባዖንም ሰዎች በጌልገላ ወደ ሰፈረው ወደ ኢያሱ፣ “በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው ተሰልፈውብናል፤ እኛን ባሮችህን አትተወን፤ ርዳን፤ ፈጥነህ በመድረስም አድነን” ሲሉ ላኩበት።
7ስለዚህ ኢያሱ ምርጥ የሆኑትን ተዋጊዎች ሁሉ ጨምሮ ሰራዊቱን በሙሉ ይዞ ከጌልገላ ወጣ። 8እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “አትፍራቸው፤ ሁሉንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻቸዋለሁ፤ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም” አለው።
9ኢያሱ ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሥ ዐድሮ ድንገት ወረራቸው። 10እግዚአብሔርም የአሞራውያንን ነገሥታት በእስራኤል ፊት አሸበራቸው፤ በገባዖን እጅግ መታቸው፤ ወደ ቤትሖሮን በሚያስወጣውም መንገድ ሽቅብ ተከተላቸው፤ እስከ ዓዜቅና እስከ መቄዳም ድረስ አሳድዶ መታቸው። 11ከቤትሖሮን ወደ ዓዜቃ ቍልቍል በሚወስደው መንገድ ላይ፣ ከእስራኤላውያን ፊት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሰማይ ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ በእስራኤላውያን ሰይፍ ካለቁት ይልቅ በወረደው የበረዶ ድንጋይ ያለቁት በልጠው ተገኙ።
12 እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤል አሳልፎ በሰጠባት ዕለት፣ ኢያሱ እግዚአብሔርን በእስራኤል ፊት እንዲህ አለው፤
“ፀሓይ ሆይ፤ በገባዖን ላይ ቁሚ፤
ጨረቃም ሆይ፤ በኤሎን ሸለቆ ላይ ቀጥ በዪ።”
13ስለዚህ ሕዝቡ ጠላቶቹን እስኪበቀል
ድረስ#10፥13 ወይም ሕዝቡ እስኪያሸንፍ ድረስ፣ ፀሓይ ባለችበት ቆመች፤
ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም።
ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል።
ፀሓይ በሰማዩ መካከል ቆመች፤ ለመጥለቅም ሙሉ ቀን ፈጀባት። 14እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ዕለት ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ተዋግቶ ነበርና።
15ከዚያም ኢያሱ ከመላው እስራኤል ጋራ ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።
ዐምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ተገደሉ
16በዚህ ጊዜ ዐምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተደብቀው ነበር። 17ኢያሱም ዐምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸውን ሰማ፤ 18እንዲህም አለ፤ “ትልልቅ ድንጋዮች ወደ ዋሻው አፍ አንከባልሉ፤ ጠባቂ ሰዎችንም በዚያ አቁሙ፤ 19ጠላቶቻችሁን አሳድዷቸው እንጂ ችላ አትበሉ፤ ከበስተ ኋላ ሆናችሁም አደጋ ጣሉባቸው፤ ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሏቸው፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና።”
20ስለዚህ ኢያሱና እስራኤላውያን እስከ መጨረሻው ደመሰሷቸው፤ የተረፉት ጥቂቶቹ ግን ወደ ተመሸጉት ከተሞቻቸው ለመድረስ ቻሉ። 21ከዚያም ሰራዊቱ ሁሉ በደኅና ተመልሶ፣ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ መጣ፤ በእስራኤላውያንም ላይ አንዲት ቃል የተናገረ ሰው አልነበረም።
22ኢያሱም፤ “ዋሻውን ከፍታችሁ እነዚያን ዐምስቱን ነገሥታት አውጥታችሁ አምጡልኝ” አላቸው። 23እነርሱም ዐምስቱን ነገሥታት ማለትም የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፣ የኬብሮንን ንጉሥ፣ የያርሙትን ንጉሥ፣ የለኪሶን ንጉሥ የዔግሎንን ንጉሥ አውጥተው አመጡለት። 24እነዚህን ነገሥታት ባመጡለትም ጊዜ፣ ኢያሱ መላውን የእስራኤልን ወንዶች ከጠራ በኋላ ዐብረውት የመጡትን የጦር አዛዦች፣ “ወደዚህ ቅረቡና እግሮቻችሁን በእነዚህ ነገሥታት ዐንገት ላይ አድርጉ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ፊት ቀርበው እግራቸውን በነገሥታቱ ዐንገት ላይ አሳረፉ።
25ኢያሱም፣ “አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በርቱ፤ ጽኑ፤ እንግዲህ በምትወጓቸው ጠላቶች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር እንደዚሁ ያደርጋልና” አላቸው። 26ከዚያም ኢያሱ ነገሥታቱን መትቶ ገደላቸው፤ በዐምስትም ዛፎች ላይ ሰቀላቸው፤ ሬሳቸውም እስኪመሽ ድረስ አልወረደም ነበር።
27ፀሓይ ለመጥለቅ በማዘቅዘቅ ላይ ሳለች ኢያሱ ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም የነገሥታቱን ሬሳ ከዛፎቹ ላይ አውርደው ቀድሞ ተደብቀው ወደ ነበሩበት ዋሻ ውስጥ ጣሏቸው። በዋሻውም አፍ ትልልቅ ድንጋዮች አኖሩ፤ ድንጋዮቹም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ።
28በዚያች ዕለት ኢያሱ መቄዳን ያዘ፤ ከተማዪቱንና ንጉሧንም በሰይፍ ስለት መታ፤ አንድም ሰው ሳያስቀር በውስጧ ያለውን ሁሉ ፈጽሞ ደመሰሰ፤ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ያደረገውንም ሁሉ፣ በመቄዳ ንጉሥ ላይ አደረገ።
የደቡብ ከተሞች መያዝ
29ከዚያም ኢያሱና ከርሱ ጋራ የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከመቄዳ ወደ ልብና ዐለፉ፤ ወጓትም። 30እንዲሁም እግዚአብሔር ከተማዪቱንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። ኢያሱ ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ በሰይፍ ስለት አጠፋ፤ አንድም ሰው አላስተረፈም። በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ያደረገውንም በልብና ንጉሥ ላይ ደገመው።
31ከዚያም ኢያሱና ከርሱ ጋራ የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከልብና ወደ ለኪሶ ዐለፉ፤ ወጓትም። 32እግዚአብሔር ለኪሶን አሳልፎ ለእስራኤል ሰጠ፤ ኢያሱም በሁለተኛው ቀን ያዛት፤ በልብና እንዳደረገው ሁሉ እዚህም ከተማዪቱንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጃቸው። 33በዚህ ጊዜ የጌዝር ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት መጣ፤ ኢያሱ ግን አንድ እንኳ ሳያስተርፍ ንጉሡንና ሕዝቡን መታቸው።
34ከዚያም ኢያሱና ከርሱ ጋራ የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከለኪሶ ወደ ዔግሎን ዐለፉ፤ ወጓትም። 35በዚያ ዕለት ያዟት፤ በሰይፍም ስለት አጠፏት፤ በለኪሶ እንዳደረጉት ሁሉ እዚህም በውስጧ የሚገኙትን ፈጽመው ደመሰሷቸው።
36ከዚያም ኢያሱና ከርሱ ጋራ የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከዔግሎን ወደ ኬብሮን ወጡ፤ ወጓትም። 37ከተማዪቱንም ከንጉሧ፣ ከመንደሮቿና በውስጧ ካሉት ጋራ ሁሉ አንድም ሰው ሳያስቀሩ በሰይፍ ስለት ፈጇቸው፤ በዔግሎን እንዳደረጉት ሁሉ እዚህም ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ ፈጽመው ደመሰሱ።
38ከዚያም ኢያሱና ከርሱ ጋራ የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ኋላ ተመልሰው ዳቤርን ወጓት። 39ከተማዪቱን፣ ንጉሧንና መንደሮቿን ይዘው በሰይፍ ስለት ፈጇቸው፤ በውስጧ ያለውንም ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ ደመሰሱ፤ በልብናና በንጉሧ እንዲሁም በኬብሮን ያደረጉትን ሁሉ እዚህም በዳቤርና በንጉሧ ላይ ደገሙት።
40በዚህ ሁኔታም ኢያሱ ተራራማውን አገር ኔጌብን፣ የምዕራቡን ቈላና የተራራውን ሸንተረሮች ጨምሮ ምድሪቱን በሙሉ ከነገሥታቷ ጋራ ያዘ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት፣ እስትንፋስ ያላቸውን ሁሉ ፈጽሞ ደመሰሰ፤ ማንንም በሕይወት አላስቀረም። 41ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ እንዲሁም የጎሶምን ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ በሙሉ ያዘ። 42ኢያሱ እነዚህን ሁሉ ነገሥታትና ምድራቸውን ያሸነፈው በአንድ ዘመቻ ብቻ ነበር፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ተዋግቶላቸዋልና።
43ከዚህ በኋላ ኢያሱ ከመላው እስራኤላውያን ጋራ ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።
Currently Selected:
ኢያሱ 10: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.