የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢያሱ 18

18
የቀሪው ምድር መከፋፈል
1መላው የእስራኤላውያን ማኅበር በሴሎ ተሰበሰቡ፣ የመገናኛውንም ድንኳን እዚያው ተከሉ፤ ምድሪቱም ጸጥ ብላ ተገዛችላቸው። 2ዳሩ ግን ርስት ገና ያልተሰጣቸው ሰባት የእስራኤል ነገዶች ነበሩ።
3ስለዚህ ኢያሱ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ለመውረስ ቸል የምትሉት እስከ መቼ ነው? 4አሁንም ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ሰው ምረጡ፤ እኔም ምድሪቱን ተዘዋውረው እንዲያጠኑና እያንዳንዱም ነገድ መውረስ የሚገባውን ድርሻ ዝርዝር መግለጫ ጽፈው እንዲያመጡ እልካቸዋለሁ፤ ከዚያም ወደ እኔ ይመለሳሉ። 5ምድሪቱንም ሰባት ቦታ ይከፍሏታል፤ ይሁዳ በደቡብ፣ የዮሴፍ ዘሮች በሰሜን በኩል የተመደበላቸውን ርስት ይዘው ይኖራሉ። 6የሰባቱን የመሬት ክፍፍል ዝርዝር መግለጫ ጽፋችሁ ወደ እኔ ታመጡና በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ። 7ሌዋውያኑ ግን ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ርስታቸው ስለ ሆነ በእናንተ መካከል ድርሻ አይኖራቸውም። ጋድ፣ ሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምሥራቅ ዮርዳኖስ የሰጣቸውን ርስት ቀደም አድርገው ወስደዋል።”
8ሰዎቹ የምድሪቱን ሁኔታ ለማጥናትና ለመመዝገብ ጕዞ ሲጀምሩ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ የምድሪቱን ሁኔታ አጥኑና በዝርዝር ከጻፋችሁ በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም እዚሁ ሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ” አላቸው። 9ስለዚህም ሰዎቹ ሄደው ምድሪቱን ተዘዋውረው አዩ፤ ከነ ከተሞቿም ሰባት ቦታ ከፍለው በጥቅልል ብራና ላይ በዝርዝር ጻፉ፤ ከዚያም በሴሎ ሰፈር ወዳለው ወደ ኢያሱ ተመለሱ።
10ኢያሱም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ ጣለላቸው፤ ምድሪቱንም እንደየነገዱ ደልድሎ ለእስራኤላውያን አከፋፈላቸው።
ለብንያም ነገድ የተመደበው ድርሻ
11ለብንያም ነገድ የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ። በዕጣ የደረሳቸውም ምድር የሚገኘው በይሁዳና በዮሴፍ ነገዶች ርስት መካከል ሲሆን እንደሚከተለው ነው፤
12በሰሜን ያለው ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ይነሣና የኢያሪኮን ሰሜናዊ ተረተር ዐልፎ፣ በስተ ምዕራብ ወዳለው ኰረብታማ ምድር በማምራት፣ እስከ ቤትአዌን ምድረ በዳ ይዘልቃል። 13ከዚያ ደግሞ ወደ ደቡብ ሎዛ ማለት ወደ ቤቴል ተረተር ይሻገርና በታችኛው ቤትሖሮን በስተ ደቡብ ባለው ተራራ በኩል አድርጎ ወደ አጣሮት አዳር ይወርዳል።
14በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ከቤትሖሮን ትይዩ ካለው ኰረብታ ተነሥቶ፣ በምዕራብ በኩል ወደ ደቡብ በመታጠፍ፣ የይሁዳ ነገድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ቂርያትበኣል ማለት ወደ ቂርያትይዓይሪም ያልፋል፤ ይህ እንግዲህ በምዕራብ በኩል ያለው ድንበር ነው።
15በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ደግሞ በምዕራብ በኩል ከቂርያትይዓይሪም ጥግ ይነሣና እስከ ኔፍቶ ውሃ ምንጭ ይዘልቃል፤ 16ይኸው ድንበር ከራፋይም ሸለቆ በስተሰሜን ባለው በሄኖም ሸለቆ ትይዩ ቍልቍል ወደ ኰረብታው ግርጌ ይወርዳል፤ ከዚያም ከኢያቡሳውያን ከተማ በደቡብ በኩል ባለው ተረተር አድርጎ ወደ ሄኖም ሸለቆ በመውረድ እስከ ዓይንሮጌል ይዘልቃል። 17ደግሞም ወደ ሰሜን ይታጠፍና በዓይንሳሚስ በኩል አድርጎ እስከ ጌሊሎት ይዘልቃል፤ ከዚያም በአዱሚም መተላለፊያ ትይዩ እስካለው እስከ ሮቤል ልጅ እስከ ቦሀን ድንጋይ ይወርዳል። 18ወደ ቤትዓረባ ሰሜናዊ ተረተር በመቀጠል ቍልቍል ወደ ዓረባ ይወርዳል። 19ከዚያም ሰሜናዊውን የቤትሖግላንን ተረተር ዐልፎ ይሄድና በስተ ደቡብ የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚገባበት እስከ ጨው ባሕር ወሽመጥ ይዘልቃል፤ ይህም ደቡባዊ ድንበሩ ነው።
20በምሥራቅ በኩል ያለው ድንበር፣ ራሱ የዮርዳኖስ ወንዝ ነው።
ይህ እንግዲህ የብንያም ነገድ ጐሣዎች በርስትነት የወረሷት ምድር ዳር ድንበሮቿ ሁሉ እነዚህ ነበሩ።
21የብንያም ነገድ በየጐሣቸው የያዟቸው ከተሞች እነዚህ ናቸው፤
ኢያሪኮ፣ ቤትሖግላ፣ ዓመቀጺጽ፣ 22ቤትዓረባ፣ ጽማራይም፣ ቤቴል፣ 23ዓዊም፣ ዖፍራ፣ ኤፍራታ፣ 24ክፊርዓሞናይ፣ ዖፍኒ እንዲሁም ጌባዕ ናቸው፤ እነዚህም ከነመንደሮቻቸው ዐሥራ ሁለት ከተሞች ናቸው።
25ገባዖን፣ ራማ፣ ብኤሮት፣ 26ምጽጳ፣ ከፊራ፣ አሞቂ፣ 27ሬቄም፣ ይርጵኤል፣ ተርአላ፣ 28ጼላ ኤሌፍ፣ የኢያቡሳውያን ከተማ ኢየሩሳሌም፣ ጊብዓ እንዲሁም ቂርያት ነበሩ፤ እነዚህም ከነመንደሮቻቸው ዐሥራ አራት ከተሞች ናቸው።
እንግዲህ የብንያም ነገድ በየጐሣቸው የወረሱት ይህ ነበር።

Currently Selected:

ኢያሱ 18: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ