ኢያሱ 23
23
ኢያሱ ለመሪዎች የተናገረው የመሰናበቻ ቃል
1 እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው እነሆ፣ ብዙ ዘመን ዐለፈ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በጣም አርጅቶ፣ ዕድሜውም ገፍቶ ነበር። 2ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ አለቆቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ፈራጆቻቸውንና ሹማምታቸውን በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቷል። 3አምላካችሁ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ሲል በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረገውን ማንኛውንም ነገር እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋላችሁ ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው። 4ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር#23፥4 የሚድትራንያን ባሕር ነው። ድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ። 5ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።
6“በርቱ፤ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ። 7በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋራ አትተባበሩ፤ የአማልክታቸውን ስም አትጥሩ፤ አትማሉባቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ 8ነገር ግን እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አጥብቃችሁ ያዙ።
9“እግዚአብሔር ታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቷቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። 10አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት የሚዋጋላችሁ ስለ ሆነ፣ ከእናንተ አንዱ ሰው ሺሑን ያሳድዳል። 11ስለዚህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለመውደድ ተጠንቀቁ።
12“ነገር ግን ከርሱ ተመልሳችሁ ተርፈው በመካከላችሁ ከሚገኙት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋራ ብትተባበሩ፣ በጋብቻም ብትተሳሰሩና ብትቀላቀሉ፣ 13አምላካችሁ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ከእንግዲህ ከፊታችሁ እንደማያወጣቸው ይህን ልታውቁ ይገባል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስም ወጥመድና እንቅፋት፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ፣ ለዐይኖቻችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል።
14“እነሆ፤ አሁን የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሟል። 15ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁ መልካሙ ተስፋ በሙሉ እንደ ተፈጸመ ሁሉ፣ እንደዚሁም አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉውን ነገር ያመጣባችኋል። 16አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ኪዳን ብታፈርሱ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብትሰግዱላቸው የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ይነድዳል፤ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”
Currently Selected:
ኢያሱ 23: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.