ኢያሱ 4
4
1ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ፣ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ 2“ከሕዝቡ መካከል ከየነገዱ አንዳንድ ሰው፣ በድምሩ ዐሥራ ሁለት ሰው ምረጥ፤ 3እንዲሁም ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ልክ ካህናቱ ከቆሙበት ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ አንሥተው በመሸከም ከእናንተ ጋራ እንዲሻገሩና ዛሬ በምታድሩበት ቦታ እንዲያኖሯቸው ንገራቸው።”
4ስለዚህ ኢያሱ ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ የሾማቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ፤ 5እንዲህም አላቸው፤ “ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዕለፉ፤ እያንዳንዳችሁም በእስራኤል ነገድ ቍጥር አንዳንድ ድንጋይ በትከሻችሁ ተሸከሙ፤ 6ይህም በመካከላችሁ ምልክት እንዲሆናችሁ ነው። ወደ ፊት ልጆቻችሁ፣ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው ቢጠይቋችሁ፣ 7የዮርዳኖስ ወንዝ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት መቆሙን፣ እንዲሁም ታቦቱ ዮርዳኖስን በሚሻገርበት ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መቆሙን፣ እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ሕዝብ የዘላለም መታሰቢያ መሆናቸውን ንገሯቸው።”
8እስራኤላውያንም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረውም መሠረት፣ በእስራኤል ነገዶች ቍጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል አነሡ፤ ወደ ሰፈራቸውም ይዘው በመሻገር በዚያ አኖሯቸው። 9ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ቆመውበት በነበረው በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ሌሎች ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን አቆመ፤ እነዚህም ድንጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ#4፥9 ወይም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አቆመ በዚሁ ስፍራ ይገኛሉ።
10ሙሴ ለኢያሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲነግር ኢያሱን ያዘዘው እስኪፈጸም ድረስ፣ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ቈዩ፤ ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ፤ 11ሕዝቡ ሁሉ ተሻግረው እንዳበቁ፣ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ፣ ሕዝቡ እያዩአቸው ተሻገሩ። 12የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ፣ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእስራኤላውያን ፊት ቀድመው ተሻገሩ። 13አርባ ሺሕ ያህሉ ጦርና ጋሻቸውን ይዘው፣ ለውጊያ ዝግጁ ሆነው፣ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ።
14በዚያች ዕለት እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤ ሕዝቡ ሙሴን እንዳከበሩት ሁሉ፣ ኢያሱንም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አከበሩት።
15ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ 16“የምስክሩን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ እዘዛቸው።”
17ኢያሱም ካህናቱን “ከዮርዳኖስ ውጡ” ብሎ አዘዛቸው።
18ካህናቱ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ከውሃው በመውጣት እግራቸው ደረቁን መሬት ልክ ሲነካ የዮርዳኖስ ውሃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፤ እንደ ቀድሞው ሁሉ ሞልቶ በዳሩ ሁሉ ይፈስስ ጀመር።
19የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ሕዝቡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ በኢያሪኮ ምሥራቃዊ ዳርቻ በጌልገላ ሰፈረ። 20ኢያሱም ከዮርዳኖስ ወንዝ ያወጧቸውን ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች በጌልገላ ተከላቸው፤ 21እስራኤላውያንንም እንዲህ አላቸው፤ “ልጆቻችሁ ወደ ፊት፣ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው አባቶቻቸውን ቢጠይቁ፣ 22‘እስራኤል ይህን ዮርዳኖስ በደረቅ ምድር ተሻገረ’ ብላችሁ ንገሯቸው፤ 23እኛ እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን#4፥23 ዕብራይስጡ ያም ሱፍ ይላል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው። እንዳደረቀው ሁሉ፣ እናንተም እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ በፊታችሁ አደረቀው። 24ይህን ያደረገውም፣ የእግዚአብሔር ክንድ ብርቱ መሆኑን የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንዲያውቁና እናንተም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለዘላለም እንድትፈሩ ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.