ዘሌዋውያን 26
26
በመታዘዝ የሚገኝ በረከት
1“ ‘ትሰግዱላቸው ዘንድ ጣዖታትን አታብጁ፤ ምስል ወይም የማምለኪያ ዐምድ አታቁሙ፤ በምድራችሁም ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
2“ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3“ ‘በሥርዐቴ ብትሄዱ፣ ትእዛዜንም በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣ 4ዝናብን በወቅቱ እሰጣችኋለሁ፤ ምድሪቱ እህሏን፣ የሜዳ ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። 5የምትወቁት እህል፣ የወይን ዘለላ እስከምትቈርጡበት ጊዜ፣ የምትቈርጡትም የወይን ዘለላ፣ እህል እስከምትዘሩበት ጊዜ ያደርሷችኋል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ።
6“ ‘በምድሪቱ ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ ማንም አያስፈራችሁም። ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። 7ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነርሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 8ከእናንተ ዐምስቱ መቶውን፣ መቶውም ዐሥሩን ሺሕ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
9“ ‘ፊቴን ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ እንድታፈሩና እንድትበዙም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋራ አጸናለሁ። 10የዓምናውን እህል እየበላችሁ ከጐተራው ሳያልቅ ለዘንድሮው እህል ደግሞ ቦታ ታስለቅቃላችሁ። 11ማደሪያዬን#26፥11 ወይም የመገናኛ ድንኳኔን በመካከላችሁ አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። 12በመካከላችሁ እመላለሳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ። 13ለግብጻውያን ባሪያዎች እንዳትሆኑ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነት ቀንበራችሁን ሰብሬ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።
አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት
14“ ‘ነገር ግን ባትሰሙኝ፣ እነዚህን ትእዛዞች ባትጠብቁ፣ 15ሥርዐቴን ብትንቁ፣ ሕጌን ብታቃልሉ፣ ትእዛዞቼንም ሁሉ ባለመፈጸም ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፣ 16እኔም ይህን አደርግባችኋለሁ፤ ድንገተኛ ድንጋጤ፣ የሚቀሥፍ በሽታ፣ ዐይናችሁን የሚያጠፋና ሰውነታችሁን የሚያመነምን ትኵሳት አመጣባችኋለሁ፤ እህል የምትዘሩት በከንቱ ነው፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። 17በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ።
18“ ‘ከዚህ ሁሉ በኋላ ባትታዘዙኝ፣ ስለ ኀጢአታችሁ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ፤ 19የትዕቢታችሁን ኀይል እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። 20ኀይላችሁ በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁ እህሏን፣ የምድሪቱ ዛፎችም ፍሬዎቻቸውን አይሰጡምና።
21“ ‘በእኔ ላይ ማመፅ ብትቀጥሉና ባትታዘዙኝ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን ሰባት ዕጥፍ መቅሠፍት እጨምርባችኋለሁ። 22የዱር አራዊትን እሰድድባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁን ይነጥቋችኋል፤ ከብቶቻችሁን ያጠፉባችኋል፤ ቍጥራችሁ ይመነምናል፤ መንገዶቻችሁም ሰው አልባ ይሆናሉ።
23“ ‘በዚህ ሁሉ ግን ወደ እኔ ባትመለሱ፣ በእኔም ላይ ማመፃችሁን ብትቀጥሉ 24እኔም ጠላት እሆንባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም ሰባት ዕጥፍ አስጨንቃችኋለሁ። 25ቃል ኪዳኔን ስላፈረሳችሁ፣ በላያችሁ ሰይፍ በማምጣት እበቀላችኋለሁ፤ በከተሞቻችሁ ውስጥ በምትሰበሰቡበት ጊዜ ቸነፈር እሰድድባችኋለሁ፤ ለጠላትም እጅ ዐልፋችሁ ትሰጣላችሁ። 26የእንጀራችሁ እህል እንዲቋረጥ በማደርግበት ጊዜ፣ ዐሥር ሴቶች በአንድ ምጣድ ላይ እንጀራ ይጋግራሉ፤ እንጀራውንም በሚዛን መዝነው እናንተም ትበላላችሁ፤ ግን አትጠግቡም።
27“ ‘በዚህ ሁሉ ግን ባትታዘዙኝ፣ በእኔም ላይ ማመፃችሁን ብትቀጥሉ፣ 28እኔም በቍጣዬ እመጣባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም እኔው ራሴ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29የወንዶች ልጆቻችሁን ሥጋና የሴቶች ልጆቻችሁን ሥጋ ትበላላችሁ። 30የኰረብታ መስገጃዎቻችሁን እደመስሳለሁ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁን አፈርሳለሁ፤ በድኖቻችሁን በድን በሆኑት ጣዖቶቻችሁ ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። 31ከተሞቻችሁን አፈራርሳለሁ፤ መቅደሶቻችሁንም ወና አደርጋለሁ፤ ጣፋጭ ሽታ ያለውን መሥዋዕታችሁንም አልቀበልም። 32በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻችሁ እስኪደነቁ ድረስ፣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ። 33በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ሰይፌን መዝዤም አሳድዳችኋለሁ። ምድራችሁ ባድማ፣ ከተሞቻችሁም ፍርስራሽ ይሆናሉ። 34ምድሪቱ ባድማ በሆነችበት ጊዜ ሁሉና እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር በምትኖሩበት ወቅት ምድሪቱ በሰንበት ዓመቷ ትደሰታለች፤ ምድሪቱም በሰንበቷ ታርፋለች፤ ትደሰታለችም። 35ምድሪቱ እናንተ በነበራችሁባት ጊዜ በሰንበት ያላገኘችውን ዕረፍት፣ ባድማ በምትሆንበት ጊዜ ሁሉ ታገኛለች።
36“ ‘ከእናንተ በሕይወት የተረፉትን፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ድንጋጤ እሰድድባቸዋለሁ፤ ነፋስ የሚያንቀሳቅሰው የቅጠል ድምፅ ያስበረግጋቸዋል፤ የሚያሳድዳቸውም ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሮጣሉ፤ ይወድቃሉም። 37የሚያሳድዳቸው ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት መቆም አትችሉም። 38በአሕዛብ መካከል ታልቃላችሁ፤ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። 39ከእናንተ የተረፉት በጠላቶቻቸው ምድር በራሳቸው ኀጢአትና በአባቶቻቸው ኀጢአት ምክንያት መንምነው ያልቃሉ።
40“ ‘ነገር ግን ለእኔ ያልታመኑበትንና በእኔም ላይ ያመፁበትን የራሳቸውን ኀጢአትና የአባቶቻቸውን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ 41ይኸውም፣ እኔ ጠላት እንድሆንባቸውና ወደ ጠላቶቻቸው ምድር እንድሰድዳቸው ያደረገኝን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድና ስለ ኀጢአታቸው የሚገባውን ቅጣት ቢቀበሉ፣ 42በዚያ ጊዜ ከያዕቆብ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ከይሥሐቅም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ደግሞም ከአብርሃም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ ምድሪቱንም ዐስባታለሁ። 43ምድሪቱ እነርሱ ለቅቀዋት ስለ ሄዱ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱ በሌሉበት ጊዜም ባድማ ሆና በሰንበቷ ትደሰታለች፤ ሕጌን በማቃለላቸውና ሥርዐቴን በመናቃቸው፣ የኀጢአታቸውን ቅጣት ይቀበላሉ። 44በዚህ ሁሉ ግን ከእነርሱ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን በማፍረስ፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ፈጽሜ እስካጠፋቸው ድረስ አልተዋቸውም፤ አልጸየፋቸውምም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ። 45ስለ እነርሱም ስል፣ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው ጋራ የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”
46 እግዚአብሔር በራሱና በእስራኤላውያን መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ በኩል ያቆማቸው ሥርዐቶች፣ ሕጎችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.