ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሀብታም ሰው አንድ መጋቢ ነበረው፤ ይኸው መጋቢ የሀብታሙን ሰው ንብረት እንደሚያባክን ለዚሁ ሰው ወሬ ደረሰው። ስለዚህ አስጠራውና፣ ‘ይህ የምሰማብህ ምንድን ነው? ከእንግዲህ አንተ መጋቢ ልትሆነኝ ስለማትችል፣ የምታስተዳድረውን ንብረት መቈጣጠሪያ ሒሳብ አስረክበኝ’ አለው። “መጋቢውም በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ከመጋቢነት ሊሽረኝ ነው፤ ለማረስ ጕልበት የለኝም፤ መለመን ደግሞ ዐፍራለሁ፤ ስለዚህ ምን ላድርግ? ከመጋቢነት የተሻርሁ እንደ ሆነ፣ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን ዐውቃለሁ።’ “ስለዚህ የጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ጠራ፤ የመጀመሪያውንም ሰው ‘የጌታዬ ዕዳ ምን ያህል አለብህ?’ አለው። “እርሱም፣ ‘አንድ መቶ ማድጋ ዘይት አለብኝ’ አለ። “መጋቢውም፣ ‘የውል ወረቀትህን ዕንካ፤ ቶሎ ተቀምጠህ “ዐምሳ ማድጋ” ብለህ ጻፍ’ አለው። “ከዚያም ሌላውን፣ ‘አንተስ ስንት አለብህ?’ አለው። “እርሱም፣ ‘ዐምሳ ዳውላ ስንዴ’ አለው። “መጋቢውም፣ ‘የብድር ደብዳቤህን ዕንካ፤ “አርባ ዳውላ” ብለህ ጻፍ’ አለው። “ጌታውም አጭበርባሪውን መጋቢ በብልኅነቱ አደነቀው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ከመሰሎቻቸው ጋራ በሚኖራቸው ግንኙነት ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የዚህ ዓለም ገንዘብ ባለቀ ጊዜ በዘላለም ቤት ተቀባይነት እንዲኖራችሁ፣ በዚሁ ገንዘብ ወዳጆችን ለራሳችሁ አፍሩበት። “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም። እንግዲህ፣ በዚህ ዓለም ሀብት ካልታመናችሁ፣ እውነተኛውንማ ሀብት ማን ዐደራ ብሎ ይሰጣችኋል? በሌላው ሰው ሀብት ካልታመናችሁ፣ የራሳችሁ የሆነውን ሀብት ማን ይሰጣችኋል? “ማንም ባሪያ ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።”
ሉቃስ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 16
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 16:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos