ማቴዎስ 21
21
ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ
21፥1-9 ተጓ ምብ – ማር 11፥1-10፤ ሉቃ 19፥29-38
21፥4-9 ተጓ ምብ – ዮሐ 12፥12-15
1ኢየሩሳሌም መቃረቢያ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደተባለችው ስፍራ እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ 2እንዲህ አላቸው “በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፤ እንደ ደረሳችሁም አንዲት አህያ ከነውርንጫዋ ታስራ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም ወደ እኔ አምጧቸው። 3ማንም ሰው ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልጋሉ፤ እርሱም ወዲያውኑ መልሶ ይልካቸዋል’ በሉት።”
4ይህ የሆነውም በነቢዩ እንዲህ በማለት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።
5“ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፤
‘እነሆ፤ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፣
በአህያዪቱና በግልገሏ፣
በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።’ ”
6ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7አህያዪቱንና ውርንጫዋን አምጥተው ልብሶቻቸውን በላያቸው ላይ አኖሩ፤ እርሱም ተቀመጠባቸው። 8ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሶቻቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎቹም ከዛፎች ቅርንጫፍ እየዘነጠፉ በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ነበር። 9ቀድሞት የሚሄደውና ይከተለው የነበረው ሕዝብም እንዲህ እያለ ይጮኽ ነበር፤
“ሆሳዕና#21፥9 በዕብራይስጡ አገላለጽ አሁን አድን! ማለት ሲሆን የምስጋና አገላለጽ ነው፤ 15 ይመ፤ ለዳዊት ልጅ!”
“በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!”#21፥9 መዝ 118፥25-26
“ሆሳዕና በአርያም!”
10ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፣ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች።
11ሕዝቡም፣ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ።
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲነግዱ ያገኛቸውን አስወጣቸው
21፥12-16 ተጓ ምብ – ማር 11፥15-18፤ ሉቃ 19፥45-47
12ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ በመገለባበጥ፣ 13“ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’#21፥13 ኢሳ 56፥7 ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን፣ ‘የወንበዴዎች ዋሻ’#21፥13 ኤር 7፥11 አደረጋችሁት” አላቸው።
14በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። 15ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሳዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ በመቅደስ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ።
16እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት።
ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?
“ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣
ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ” # 21፥16
መዝ 8፥2
17ትቷቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው ዐደረ።
ፍሬ አልባ የሆነችው በለስ
21፥18-22 ተጓ ምብ – ማር 11፥12-14፤ 11፥20-24
18ኢየሱስ በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመለስ ላይ ሳለ ተራበ፤ 19በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ፍሬ አይኑርብሽ!” አላት፤ የበለሷም ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች።
20ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ፣ “የበለሷ ዛፍ እንዴት በአንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ።
21ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆናል፤ 22አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።”
በኢየሱስ ሥልጣን ላይ የቀረበ ጥያቄ
21፥23-27 ተጓ ምብ – ማር 11፥27-33፤ ሉቃ 20፥1-8
23ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀርበው፣ “ይህን ሁሉ ነገር የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።
24ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ መልሱን ብትነግሩኝ፣ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ 25የዮሐንስ ጥምቀት የመጣው ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰው?”
እነርሱም እርስ በርስ በመነጋገር እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው?’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ 26‘ከሰዎች ነው’ ብንል ደግሞ፣ ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ሆነ ስለሚቈጥር እንፈራለን።”
27ስለዚህ ለኢየሱስ፣ “አናውቅም” ብለው መለሱለት።
እርሱም፣ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።
የመታዘዝ ትርጕም
28ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ምን ይመስላችኋል? ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበረ፤ ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ፣ ‘ልጄ ሆይ፤ ዛሬ ወደ ወይኑ ቦታ ሄደህ ሥራ’ አለው።
29 “ልጁም፣ ‘አልሄድም’ አለው፤ ኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ።
30 “ወደ ሁለተኛው ልጁ ሄዶ እንደዚያው አለው፤ ልጁም ‘ዕሺ ጌታዬ እሄዳለሁ’ አለው፤ ነገር ግን ሳይሄድ ቀረ።
31 “ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?”
እነርሱም፣ “የመጀመሪያው ልጅ” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል፤ 32መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ወደ እናንተ መጣ፤ እናንተ አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑት። የሆነውን ካያችሁ በኋላ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።
የወይን ዕርሻ ገበሬዎች ምሳሌ
21፥33-46 ተጓ ምብ – ማር 12፥1-12፤ ሉቃ 20፥9-19
33 “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የዕርሻ ባለቤት የወይን ተክል ተከለ፤ በዙሪያውም ዐጥር ዐጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 34የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል ባሮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው።
35 “ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። 36እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች ባሮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። 37በመጨረሻም፣ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ።
38 “ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። 39ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት።
40 “ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?”
41እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት።
42ኢየሱስም፣
“ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣
የማእዘን ራስ # 21፥42 ወይም የማእዘን ድንጋይ ሆነ፤
ጌታ ይህን አድርጓል፤
ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን?”
አላቸው።
43 “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ 44በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ ደግሞ የሚወድቅበትን ማንኛውንም ሰው ይፈጨዋል።”#21፥44 አንዳንድ ቅጆች ቍጥር 44 የላቸውም።
45የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ የሚናገር መሆኑን ዐወቁ። 46ነገር ግን ይዘው ሊያስሩት ቢፈልጉም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ አድርጎ ይመለከት ስለ ነበር ፈሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.