“ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና። “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን? “ማንም ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም። “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሯችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስኪ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ለመሆኑ፣ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማን ነው? “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስኪ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና።
ማቴዎስ 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 6:19-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች