ነህምያ 6
6
በቅጥሩ ሥራ ላይ የተነሣ ሌላ ታቃውሞ
1እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለበሮቹ መዝጊያ ባልገጥምላቸውም እንኳ፣ ቅጥሩን መሥራቴንና የቀረ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረባዊው ጌሳምና የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ 2ሰንባላጥና ጌሳም፣ “ናና በኦኖ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች#6፥2 የዕብራይስጡ ቅጅ፣ ኬፍሪም ይላል። በአንዲቱ እንገናኝ” ሲሉ ይህችን መልእክት ላኩብኝ።
እነርሱ ግን እኔን ለመጕዳት ዐቅደው ነበር። 3እኔም፣ “ታላቅ ሥራ እየሠራሁ ስለ ሆነ፣ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ትቼው ወደ እናንተ ወርጄ ሥራው ለምን ይቆማል?” በማለት ይህን መልስ የሚያደርሱ መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላክሁ። 4አራት ጊዜም ይህንኑ ዐይነት መልእክት ላኩብኝ፤ እኔም በእያንዳንዱ ጊዜ ያንኑ መልስ ሰጠሁ።
5ከዚያም ሰንባላጥ ለዐምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤ 6የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤
“አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቷል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጧል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣ 7ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።”
8እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት።
9ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ።
እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ።
10አንድ ቀን ቤቱ በላዩ ላይ ተዘግቶበት ወደ ነበረው ወደ መሄጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ሄድሁ፤ እርሱም፣ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በርግጥም በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው” አለኝ።
11እኔ ግን፣ “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ ይደበቃል? ወይም ደግሞ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” አልሁ። 12በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦቢያና ሰንባላጥ በገንዘብ ስለ ደለሉት እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኔ እንዳልላከው ተረዳሁ። 13በገንዘብ የተገዛው እኔን ለማስፈራራት ነው፤ ይኸውም ይህን በመፈጸም ኀጢአት እንድሠራና በዚህም መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው።
14አምላኬ ሆይ፤ ስለ ፈጸሙት ድርጊት ጦቢያንና ሰንባላጥን ዐስብ፤ ሊያስፈራሩኝ የሞከሩትን ነቢያቱን ኖዓድያንና ሌሎቹን ነቢያትም ዐስብ።
የቅጥሩ ሥራ መጠናቀቅ
15ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ ዐምስተኛ ቀን፣ በዐምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ። 16ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን ሲሰሙ፣ በዙሪያችን ያሉ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፤ በራሳቸው መተማመንም አልቻሉም፤ ምክንያቱም ይህ ሥራ የተከናወነው በአምላካችን ርዳታ መሆኑን ተገንዝበዋል።
17በዚያ ጊዜ የይሁዳ መኳንንት ለጦቢያ ብዙ ደብዳቤ ይልኩ ነበር፤ ከጦቢያም መልስ ይላክላቸው ነበር። 18በይሁዳ የሚኖሩ ሰዎች ምለውለት ነበር፤ ምክንያቱም የኤራ ልጅ የሴኬንያ ዐማት ከመሆኑም በላይ ልጁ ዮሐናን የቤራክያን ልጅ የሜሱላምን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር። 19ከዚህም በተጨማሪ ስለ መልካም ሥራው በየጊዜው ይነግሩኝና እኔም ያልሁትን ይነግሩት ነበር፤ ጦቢያም እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤ ይልክብኝ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.