ዘኍልቍ 14
14
የሕዝቡ ማመፅ
1በዚያች ሌሊት ማኅበረ ሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸና አለቀሰ። 2እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሏቸው፤ “ምነው በግብጽ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! 3እግዚአብሔር ወደዚህች ምድር የሚያመጣን ለምንድን ነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ታዲያ ወደ ግብጽ መመለሱ አይሻለንም?” 4እርስ በርሳቸውም፣ “አለቃ መርጠን ወደ ግብጽ እንመለስ” ተባባሉ።
5ከዚያም ሙሴና አሮን እዚያ በተሰበሰቡት በመላው እስራኤላውያን ማኅበር ፊት በግንባራቸው ተደፉ። 6ምድሪቱን ከሰለሏት መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7ለመላው የእስራኤል ማኅበርም እንዲህ አሉ፤ “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት። 8እግዚአብሔር በእኛ ደስ ከተሠኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል። 9ብቻ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሯቸው። ጥላቸው ተገፍፏል፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋራ ነውና አትፍሯቸው።”
10መላው ማኅበር ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነጋገሩ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ክብር በመገናኛው ድንኳን ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ። 11እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው? 12በቸነፈር እመታዋለሁ፤ እደመስሰዋለሁም፤ አንተን ግን ብርቱና ታላቅ ለሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
13ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብጻውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤ 14የተደረገውንም በዚች ምድር ለሚኖሩት ሰዎች ይነግሯቸዋል። እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋራ መሆንህን፣ ደግሞም አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊት ለፊት እንደ ታየህና ደመናህ በላያቸው እንደ ሆነ፣ አንተም ቀን በደመና ዐምድ ሌሊትም በእሳት ዐምድ እፊት እፊታቸው እየሄድህ እንደ መራሃቸው ቀድሞውኑ ሰምተዋል። 15ታዲያ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ብትፈጀው ዝናህን የሰሙ ሕዝቦች፣ 16‘እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው’ ይሉሃል።
17“አሁንም እንዲህ ስትል በተናገርኸው መሠረት የጌታ ኀይል ይገለጥ፤ 18‘እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’ 19ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።”
20 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤ 21ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣ 22ክብሬን ደግሞም በግብጽና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው ካልታዘዙኝና ዐሥር ጊዜ ከተፈታተኑኝ ሰዎች አንዳቸውም፣ 23ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም። የናቀኝ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ አያያትም፤ 24አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል። 25አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው የሚኖሩ ስለ ሆነ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር#14፥25 በዕብራይስጥ ትርጕሙ ያም ሱፍ የሚል ሲሆን የሸንበቆ ባሕር ማለት ነው። መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።”
26 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 27“ይህ ክፉ ማኅበረ ሰብ በእኔ ላይ የሚያጕረመርመው እስከ መቼ ነው? የእነዚህን ነጭናጮች እስራኤላውያን ማጕረምረም ሰምቻለሁ። 28ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ስትናገሩ የሰማኋችሁን እነዚያን ነገሮች አደርግባችኋለሁ፤ 29በተደረገው ቈጠራ መሠረት፣ ሃያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናችሁና በእኔም ላይ ያጕረመረማችሁ ሁሉ በድናችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል። 30መኖሪያችሁ እንድትሆን በጽኑ ወደማልሁላችሁ ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእናንተ አንዳችሁም አትገቡባትም። 31ይማረካሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን ግን አገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትን ምድር እነርሱ ይደሰቱባታል። 32እናንተ ግን፣ በድናችሁ በዚሁ ምድረ በዳ ወድቆ ይቀራል። 33ካለማመናችሁ የተነሣ ከእናንተ የመጨረሻው በድን እዚሁ ምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ፣ ልጆቻችሁ መከራ እየበሉ አርባ ዓመት እረኞች ይሆናሉ። 34ምድሪቱን ለመሰለል በቈያችሁበት አርባ ቀን ልክ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት ተቈጥሮ ስለ ኀጢአታችሁ አርባ ዓመት መከራ ትቀበላላችሁ፤ ምን ያህል በእናንተ ላይ እንደ ተነሣሁም ታውቃላችሁ።’ 35እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አንድ ሆኖ በተነሣብኝ በዚህ ክፉ ማኅበረ ሰብ ሁሉ ላይ እነዚህን ነገሮች አደርጋለሁ፤ መጨረሻቸው በዚሁ ምድረ በዳ ይሆናል፤ እዚሁም ይሞታሉ።”
36ከዚህ በኋላ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ ልኳቸው የነበሩትና ከዚያ ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማሠራጨት ማኅበረ ሰቡ በሙሉ እንዲያጕረመርሙበት ያደረጉ፣ 37ስለ ምድሪቱም ክፉ ወሬ በማሠራጨት ተጠያቂ የሆኑት እነዚሁ ሰዎች ተቀሥፈው በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ። 38ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከተላኩት ሰዎች በሕይወት የተረፉት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ብቻ ነበሩ።
39ሙሴም ይህን ለእስራኤላውያን ሁሉ በነገራቸው ጊዜ ክፉኛ ዐዘኑ። 40በማግስቱም ጧት ማልደው ወደ ተራራማው አገር ወጡ፤ እንዲህም አሉ፣ “ኀጢአት ሠርተናል፤ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጠን ስፍራ እንወጣለን”።
41ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትጥሳላችሁ? ይህም አይሳካላችሁም! 42እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ስላይደለ አትውጡ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ፤ 43አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በዚያ ያጋጥሟችኋልና። እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁትና እርሱም ከእናንተ ጋራ ስለማይሆን በሰይፍ ትወድቃላችሁ።”
44ሙሴም ሆነ የእግዚአብሔር ታቦት ቃል ኪዳን ከሰፈር ሳይነሡ በስሜት ተገፋፍተው ብቻ ወደ ተራራማው አገር ወጡ። 45በዚህ ጊዜ በተራራማው አገር የሚኖሩት አማሌቃውያንና ከነዓናውያን ወርደው ወጓቸው፤ እስከ ሖርማ ድረስም አሳደዷቸው።
Currently Selected:
ዘኍልቍ 14: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.