ዘኍልቍ 23
23
የመጀመሪያው የበለዓም ንግር
1በለዓም፣ “እዚህ ሰባት መሠዊያ ሥራልኝ፤ ሰባት ኰርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው። 2ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ ሁለቱም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።
3ከዚያም በለዓም ባላቅን፣ “እኔ ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣ ይሆናል፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው። ከዚያም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኰረብታ ሄደ።
4እግዚአብሔር ተገናኘው፤ በለዓምም፣ “እነሆ፤ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጅቻለሁ፤ በእያንዳንዱም ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ አቅርቤአለሁ” አለው።
5 እግዚአብሔርም በበለዓም አፍ መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመልሰህ ይህን መልእክት ንገረው” አለው።
6እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋራ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው። 7ከዚያም በለዓም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤
“ባላቅ ከአራም አመጣኝ፣
የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች።
‘ና ያዕቆብን ርገምልኝ፤
መጥተህም እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።
8እግዚአብሔር ያልረገመውን፣
እኔ እንዴት ረግማለሁ?
እግዚአብሔር ያላወገዘውንስ፣
እንዴት አወግዛለሁ?
9ከዐለታማ ተራሮች ጫፍ ሆኜ አየዋለሁ፤
በከፍታዎቹም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤
ተለይቶ የሚኖረውን፣
ራሱንም ከሌሎች ሕዝቦች ጋራ የማይቈጥረውን ሕዝብ አያለሁ።
10የያዕቆብን ትቢያ ማን ቈጥሮ ይዘልቃል?
የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቈጥረዋል።
የጻድቁን ሞት እኔ ልሙት፤
ፍጻሜዬም የርሱ ዐይነት ፍጻሜ ትሁን!”
11ባላቅም በለዓምን፣ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ አመጣሁህ፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አላደረግህልኝም!” አለው።
12እርሱም መልሶ “እግዚአብሔር በአፌ ያስቀመጠውን መናገር አይገባኝምን?” አለው።
ሁለተኛው የበለዓም ንግር
13ከዚህ በኋላ ባላቅ፣ “እነርሱን ማየት ወደምትችልበት ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ፤ በእዚያም ሁሉን ሳይሆን በከፊል ብቻ ታያቸዋለህ፤ እዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ” አለው። 14ስለዚህም በፈስጋ ተራራ ጫፍ ላይ ወዳለው ወደ ጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ እዚያም ሰባት መሠዊያ ሠርቶ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።
15በለዓምም ባላቅን፣ “እርሱን ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ” አለው።
16 እግዚአብሔር በለዓምን ተገናኘው፤ በአፉም መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመለስና ይህን መልእክት ንገረው” አለው።
17እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋራ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ ባላቅም፣ “እግዚአብሔር ምን አለ?” ሲል ጠየቀው።
18ከዚያም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤
“ባላቅ ሆይ ተነሣ፤ ስማኝ፤
የሴፎር ልጅ ሆይ አድምጠኝ፤
19ይዋሽ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፤
ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፤
ተናግሮ አያደርገውምን?
ተስፋ ሰጥቶስ አይፈጽመውምን?
20እባርክ ዘንድ ትእዛዝ ተቀብያለሁ፤
እርሱ ባርኳል፤ እኔም ልለውጠው አልችልም።
21“በያዕቆብ መጥፎ ነገር አልተገኘም፤
በእስራኤልም#23፥21 በያዕቆብ ላይ ወይም በእስራኤል ላይ እንከን አለማግኘቱን ያመለክታል። ጕስቍልና አልታየም፤
እግዚአብሔር አምላኩ ከርሱ ጋራ ነው፤
የንጉሡም እልልታ በመካከላቸው ነው።
22እግዚአብሔር ከግብጽ አወጣቸው፤
ብርታታቸውም እንደ ጐሽ ብርታት ነው።
23በያዕቆብ ላይ የሚሠራ አስማት የለም፤
በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ሟርት አይኖርም፤
ለያዕቆብና ለእስራኤል፣
‘እግዚአብሔር ያደረገውን እዩ!’ ይባልላቸዋል።
24ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይነሣል፤
ያደነውን እስኪያነክት፣
የገደለውንም ደም እስኪጠጣ፣
እንደማያርፍ አንበሳ ሆኖ ይነሣል።”
25በዚህ ጊዜ ባላቅ በለዓምን፣ “እንግዲያውስ ፈጽሞ አትርገማቸው፤ ፈጽሞም አትመርቃቸው!” አለው።
26በለዓምም፣ “እግዚአብሔር የሚለኝን ሁሉ ማድረግ እንዳለብኝ አልነገርሁህምን?” ሲል መለሰለት።
ሦስተኛው የበለዓም ንግር
27ከዚህ በኋላ ባላቅ በለዓምን፣ “በል እንግዲያው ወደ ሌላ ቦታ ልውሰድህ፤ ከዚያ ሆነህ እንድትረግምልኝ ምናልባት እግዚአብሔር ይፈቅድልህ ይሆናል” አለው። 28ባላቅም በለዓምን ምድረ በዳው ቍልቍል ወደሚታይበት ወደ ፌጎር ጫፍ አወጣው።
29በለዓምም፣ “ሰባት መሠዊያዎች እዚህ ሥራልኝ፤ ሰባት ኰርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው። 30ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።
Currently Selected:
ዘኍልቍ 23: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.