ዘኍልቍ 3

3
ሌዋውያን
1 እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር፤ 2የአሮን ልጆች የበኵሩ ስም ናዳብ፣ የሌሎቹም አብዩድ አልዓዛርና ኢታምር ይባላል። 3እርሱ ለክህነት አገልግሎት የለያቸው፣ ካህናት ለመሆን የተቀቡት የአሮን ወንድ ልጆች ስም ይህ ነው፤ 4ናዳብና አብዩድ ግን በሲና ምድረ በዳ ባልተፈቀደ እሳት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ባቀረቡ ጊዜ እዚያው እፊቱ ወድቀው ሞቱ። ወንዶች ልጆች ስላልነበሯቸውም አልዓዛርና ኢታምር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን በክህነት ያገለግሉ ነበር።
5 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6“የሌዊን ነገድ አምጥተህ ካህኑን አሮንን በአገልግሎቱ እንዲረዱት ከፊቱ አቁማቸው፤ 7በመገናኛው ድንኳን የማደሪያውን አገልግሎት በመፈጸም ለርሱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ የሚያስፈልጉትን ተግባሮች ያከናውኑ፤ 8የማደሪያውን ሥራ በመሥራትና የእስራኤላውያንን ግዴታ በመወጣት የመገናኛውን ድንኳን ሁሉ ይጠብቁ። 9ሌዋውያኑን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ተለይተው ለርሱ#3፥9 ብዙ የማሶሬቲክ ቅጆች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ ጥቂት የማሶሬቲክ፣ የኦሪተ ሳምራውያንና የሰባ ሊቃናት ቅጆች ግን ለእኔ ይላሉ። ፈጽመው የተሰጡ ናቸው። 10አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ እነርሱም ክህነታቸውን ይጠብቁ፤ ሌላ ሰው ማደሪያውን ቢቀርብ ግን ይገደል።”
11 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12“እነሆ፤ በኵር ሆኖ በሚወለደው ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ወስጃለሁ፤ ስለዚህ ሌዋውያን የእኔ ናቸው፤ 13በኵር የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና። በግብጽ ምድር በኵር የሆነውን ሁሉ በመታሁ ዕለት ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ማንኛውንም የእስራኤልን በኵር ለራሴ ለይቻለሁ፤ የእኔ ይሁን። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
14 እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ምድረ በዳ፣ 15“ሌዋውያንን በየቤታቸውና በየጐሣቸው ቍጠር፤ የምትቈጥረውም አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ ነው” አለው። 16ስለዚህ ሙሴ በእግዚአብሔር ቃል በታዘዘው መሠረት እነዚህን ቈጠራቸው።
17የሌዊ ልጆች ስም
ጌርሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ነው።
18የጌርሶን ልጆች ጐሣ ስም
ሎቤኒና ሰሜኢ ነው።
19የቀዓት ጐሣዎች፤
እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮን፣ ዑዝኤል።
20የሜራሪ ጐሣዎች፤
ሞሖሊና ሙሲ።
እንግዲህ የሌዋውያን ጐሣዎች በየቤተ ሰባቸው ሲቈጠሩ እነዚህ ናቸው።
21የሊብናና የሰሜኢ ጐሣዎች ከጌርሶን ወገን ናቸው፤ እነዚህ የጌርሶን ጐሣዎች ነበሩ።
22አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ ነበር።
23የጌርሶን ጐሣዎች በምዕራብ በኩል ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ይሰፍራሉ።
24የጌርሶን ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል።
25የጌርሶናውያን ኀላፊነት በመገናኛው ድንኳን ማደሪያውንና ድንኳኑን፣ መደረቢያዎቹን እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያለውን መጋረጃ፣ 26የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ ማደሪያ ድንኳኑንና መሠዊያውን የሚጋርደውን የአደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፣ ገመዶቹንና ከነዚሁ ጋራ ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ መጠበቅ ይሆናል።
27የእንበረማውያን፣ የይስዓራውያን፣ የኬብሮናውያንና የዑዝኤላውያን ጐሣዎች ከቀዓት ወገን ናቸው፤ እነዚህ የቀዓት ጐሣዎች ነበሩ።
28አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ስምንት ሺሕ ስድስት መቶ#3፥28 የዕብራይስጡ ትርጕም ከዚህ ጋራ ይስማማል አንዳንድ የሰባ ሊቃናት ቅጆች ግን ስምንት ሺሕ ሦስት መቶ ይላሉ። ሲሆን፣
ቀዓታውያንም መቅደሱን የመጠበቅ ኀላፊነት ነበራቸው።
29የቀዓት ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ።
30የቀዓት ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊጻፋን ይሆናል።
31እነርሱም ታቦቱን፣ ጠረጴዛውን፣ መቅረዙን፣ መሠዊያዎቹን፣ ለመቅደሱ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች፣ መጋረጃዎችንና ከነዚህ ጋራ ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ይጠብቃሉ።
32ዋናው የሌዋውያን አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነው፤ እርሱም መቅደሱን ለመጠበቅ ኀላፊ በሆኑት ላይ ተሹሞ ነበር።
33የሞሖላውያንና የሙሳያውያን ጐሣዎች ከሜራሪ ወገን ናቸው፤ እነዚህም የሜራሪ ጐሣዎች ነበሩ።
34አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተቈጠሩት ወንዶች ሁሉ ብዛታቸው ስድስት ሺሕ ሁለት መቶ ነበር።
35የሜራሪም ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ይሆናል፤
የሜራሪም ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።
36ሜራሪያውያንም የማደሪያውን ድንኳን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎች፣ ምሰሶዎቹ የሚቆሙባቸውን እግሮች፣ የማደሪያ ዕቃዎችን ሁሉና ከነዚሁ ጋራ ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ለመጠበቅ ተሹመው ነበር። 37እንዲሁም የአደባባዩን ዙሪያ ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ከነካስማቸውና ከነገመዶቻቸው ይጠብቃሉ።
38ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹ ከማደሪያው ድንኳን በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይሰፍራሉ።
እነርሱም እስራኤላውያንን ወክለው ማደሪያ ድንኳኑን ለመጠበቅ ኀላፊዎች ይሆናሉ።
ወደ ማደሪያው ድንኳን የሚቀርብ ማንኛውም ሌላ ሰው ግን ይገደል።
39አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው፣ ሙሴና አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በየጐሣቸው የቈጠሯቸው የሌዋውያን ወንዶች ልጆች ጠቅላላ ብዛት ሃያ ሁለት ሺሕ ነበር።
40 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኵር ሆነው የተወለዱትን፣ አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን እስራኤላውያን ወንዶች ሁሉ ቍጠር፤ ዝርዝራቸውንም ያዝ። 41በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ከብቶች ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን ከብቶች ለእኔ አድርጋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
42ስለዚህ ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤላውያንን በኵር ሁሉ ቈጠረ፤ 43አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው በየስማቸው የተመዘገቡት ወንድ በኵሮች ሁሉ ብዛታቸው ሃያ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር።
44ደግሞም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 45“በእስራኤላውያን በኵሮች ምትክ ሌዋውያኑን፣ በከብቶቻቸውም ምትክ የሌዋውያኑን ከብቶች ውሰድ፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 46ቍጥራቸው ከሌዋውያን ቍጥር በሁለት መቶ ሰባ ሦስት በልጦ የተገኘውን እስራኤላውያን በኵሮች ለመዋጀት፣ 47ለእያንዳንዱ በኵር ክብደቱ ባለሃያ አቦሊ በሆነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል#3፥47 ዐምሳ ዐምስት ግራም ያህል ነው። ሚዛን ልክ ዐምስት ዐምስት ሰቅል ተቀበል፤ 48የተረፉትንም እስራኤላውያን ለመዋጀት ገንዘቡን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።”
49ስለዚህ ሙሴ በሌዋውያኑ ተዋጅተው ቍጥራቸው ትርፍ ከሆነው በኵሮች ላይ የመዋጃውን ገንዘብ ተቀበለ፤ 50ከእስራኤላውያን በኵሮች ላይ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ አንድ ሺሕ ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ሰቅል#3፥50 ዐሥራ ዐምስት ኪሎ ግራም ተኩል ያህል ነው። ሰበሰበ። 51ሙሴም በእግዚአብሔር ቃል በታዘዘው መሠረት የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጣቸው።

Currently Selected:

ዘኍልቍ 3: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ