ዘኍልቍ 35

35
ለሌዋውያን የተሰጡ ከተሞች
1ከኢያሪኮ#35፥1 በዕብራይስጥ የኢያሪኮ ዮርዳኖስ ማለት ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ የጥንት ስም ሳይሆን አይቀርም። ማዶ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ፣ በሞዓብ ሜዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ከሚወርሱት ርስት ላይ ለሌዋውያን የሚኖሩባቸውን ከተሞች እንዲሰጧቸው እስራኤላውያንን እዘዛቸው፤ በየከተሞቹ ዙሪያም የግጦሽ መሬት ሰጧቸው። 3ከተሞቹ ለእነርሱ መኖሪያ፣ የግጦሽ መሬቱ ለከብቶቻቸው፣ ለበግና ለፍየል መንጎቻቸውና ለሌሎቹም እንስሶቻቸው ይሆናሉ።
4“በየከተሞቹ ዙሪያ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸውም የግጦሽ መሬት ከከተማው ቅጥር አንድ ሺሕ ክንድ#35፥4 አራት መቶ ዐምሳ ሜትር ያህል ነው። ይዘረጋል። 5ከዚያም ከተማውን መካከል በማድረግ ወደ ምሥራቅ ሁለት ሺሕ ክንድ፣#35፥5 ዘጠኝ መቶ ሜትር ያህል ነው። ወደ ደቡብ ሁለት ሺሕ ክንድ፣ ወደ ምዕራብ ሁለት ሺሕ ክንድ፣ ወደ ሰሜን ሁለት ሺሕ ክንድ ከከተማው ውጭ ለካ፤ እነዚህንም ቦታዎች ለከተሞቹ የግጦሽ መሬት ያደርጓቸዋል።
የመማፀኛ ከተሞች
35፥6-34 ተጓ ምብ – ዘዳ 4፥41-4319፥1-14ኢያ 20፥1-9
6“ለሌዋውያኑ ከምትሰጧቸው ከተሞች ስድስቱ፣ ሰው የገደለ ሸሽቶ የሚጠጋባቸው መማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ፤ በተጨማሪም አርባ ሁለት ከተሞች ስጧቸው፤ 7የግጦሽ መሬቶቻቸውን ጨምሮ በጠቅላላው አርባ ስምንት ከተሞች ለሌዋውያኑ ስጧቸው። 8እስራኤላውያን ከወረሷት ምድር ላይ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ከተሞች እያንዳንዱ ነገድ እንዳለው ድርሻ መጠን ይሆናል። ብዙ ካለው ነገድ ላይ ብዙ ከተሞች እንዲሁም ጥቂት ካለው ነገድ ላይ ጥቂት ከተሞችን ውሰዱ።”
9ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 10“እስራኤላውያንን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ጊዜ፣ 11ሳያስበው ሰው የገደለ ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች እንዲሆኑ መማፀኛ ከተሞችን ምረጡ። 12እነዚህም፣ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ዘንድ ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ የሚሸሽባቸው የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ። 13እነዚህ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ስድስት ከተሞች መማፀኛ ከተሞቻችሁ ይሆናሉ። 14ስለዚህ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስቱን እንዲሁም በከነዓን ሦስቱን የመማፀኛ ከተሞች አድርጋችሁ ስጡ። 15እነዚህም ስድስት ከተሞች ሳያስበው ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው እንዲሸሽባቸው ለእስራኤላውያን፣ ለመጻተኞችና በመካከላቸው ለሚኖር ለማንኛውም ሕዝብ የመማፀኛ ቦታዎች ይሆናሉ።
16“ ‘አንድ ሰው ሌላውን እንዲሞት በብረት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል። 17ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ድንጋይ በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል። 18ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ዕንጨት በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል። 19ደም መላሹም ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው፤ ባገኘውም ጊዜ ይግደለው። 20አንድ ሰው ዐስቦበት ሌላውን በክፋት ገፍትሮ ቢጥለው ወይም እንዲሞት ሆነ ብሎ አንዳች ነገር ቢወረውርበት 21ወይም ደግሞ በጥላቻ ተነሣሥቶ በእጁ ቢመታውና ቢሞት፣ ያ ሰው በሞት ይቀጣል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም መላሹም ገዳዩን ባገኘው ጊዜ ይግደለው።
22“ ‘ነገር ግን በጥላቻ ሳይሆን እንዲያው በድንገት አንዱ ሌላውን ገፍትሮ ቢጥለው ወይም ሳያስበው አንዳች ነገር ቢወረውርበት 23ወይም መግደል የሚችል ድንጋይ ሳያይ ጥሎበት ቢሞት፣ ጠላቱ ስላልሆነና ሊጐዳውም ዐስቦ ያላደረገው ስለ ሆነ፣ 24ማኅበሩ በዚህ ሰውና በደመኛው መካከል በእነዚህ ደንቦች መሠረት ይፍረድ። 25ማኅበሩም በነፍሰ ገዳይነት የተከሰሰውን ሰው ከደመኛው እጅ በማስጣል ወደ ሸሸበት ወደ መማጸኛው ከተማ ይመልሰው፤ የተቀደሰ ዘይት የተቀባው ሊቀ ካህን እስኪሞትም ድረስ በዚያ ይቈይ።
26“ ‘ሆኖም ተከሳሹ ሰው ሸሽቶ ከተጠጋበት መማጸኛ ከተማ ክልል ከወጣ፣ 27ደም ተበቃዩም ከከተማው ውጭ ካገኘው፣ ተከሳሹን ሊገድለው ይችላል፤ በነፍሰ ገዳይነትም አይጠየቅም። 28ተከሳሹም ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ይቈይ፤ ወደ ገዛ ርስቱ መመለስ የሚችለው ከሊቀ ካህናቱ ሞት በኋላ ብቻ ነው።
29“ ‘እንግዲህ በየትኛውም በምትኖሩበት ስፍራ፣ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ የምትፈጽሟቸው ሕጋዊ ግዴታዎቻችሁ እነዚህ ናቸው።
30“ ‘ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው በሞት የሚቀጣው ምስክሮች ሲመሰክሩበት ብቻ ነው፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው በአንድ ምስክር ብቻ በሞት አይቀጣም።
31“ ‘ነፍስ ያጠፋን፣ በመግደል ወንጀል ተጠያቂ የሆነን ሰው ጉማ አትቀበሉ፤ ፈጽሞ መሞት አለበት።
32“ ‘ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ ስለ ገባ ስለ ማንኛውም ሰው የደም ዋጋ በመቀበል ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ አገሩ ተመልሶ ሄዶ እዚያ እንዲኖር አታድርጉ።
33“ ‘ደም ምድሪቱን ስለሚያረክሳት፣ ደም ለፈሰሰባትም ምድር ስርየት ሊደረግላት የሚችለው በሌላ ሳይሆን በዚያው ደሙን ባፈሰሰው ሰው ደም ብቻ በመሆኑ፣ የምትኖሩባትን ምድር በደም አታርከሷት፤ 34የምትኖሩባትን፣ እኔም የማድርባትን ምድር አታርክሷት እኔ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁና።’ ”

Currently Selected:

ዘኍልቍ 35: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ