ምሳሌ 3
3
ከጥበብ የሚገኝ የጤና በረከት
1ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤
ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤
2ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤
ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል።
3ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤
በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤
በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው።
4በዚያ ጊዜ ሞገስንና ማስተዋልን፣
በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።
5በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤
በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤
6በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤
እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።#3፥6 ወይም ጐዳናህን ያቀናልሃል
7በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤
እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።
8ይህም ለሰውነትህ ጤንነትን፣
ለዐጥንትህም ልምላሜን ያመጣልሃል።
9 እግዚአብሔርን በሀብትህ፣
ከምርትህ ሁሉ በኵራት አክብረው፤
10ይህን ብታደርግ፣ ጐተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤
መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል።
11ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤
በዘለፋውም አትመረር፤
12አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ#3፥12 ወይም እንደሚገሥጽ ሁሉ፣
እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና።
13ብፁዕ ነው፤
ጥበብን የሚያገኛት፣
ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤
14እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣
ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና።
15ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤
አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም።
16በቀኝ እጇ ረዥም ዕድሜ አለ፤
በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች።
17መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤
ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።
18ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤
የሚይዟትም ይባረካሉ።
19 እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤
በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤
20በዕውቀቱ ቀላያት ተከፈሉ፤
ደመናትም ጠልን አንጠበጠቡ።
21ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ጥበብና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤
እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤
22ለነፍስህ ሕይወት፣
ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ።
23ከዚያም መንገድህን ያለ ሥጋት ትሄዳለህ፤
እግርህም አይሰናከልም፤
24ስትተኛ አትፈራም፤
ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል።
25ድንገተኛን መከራ፣
በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤
26 እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤
እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል።
27ማድረግ እየቻልህ
ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ።
28አሁን በእጅህ እያለ፣
ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው።
29አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣
በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት።
30ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣
ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ።
31በክፉ ሰው አትቅና፤
የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ።
32 እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤
ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል።
33የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤
የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል።
34እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤
ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።
35ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤
ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.