ምሳሌ 4
4
ጥበብ ከሁሉ በላይ መሆኗ
1ልጆቼ ሆይ፤ የአባትን ምክር አድምጡ፤
ልብ ብላችሁ ስሙ፤ ማስተዋልንም ገንዘብ አድርጉ።
2በጎ ትምህርት እሰጣችኋለሁ፤
ስለዚህ ትምህርቴን አትተዉ።
3በአባቴ ቤት ገና ለግላጋ ወጣት፣
ለእናቴም አንድ ልጇ ብቻ በነበርሁ ጊዜ፣
4አባቴ እንዲህ ሲል አስተማረኝ፤
“ቃሌን በሙሉ በልብህ ያዝ፤
ትእዛዜንም ጠብቅ፤ በሕይወት ትኖራለህ።
5ጥበብን አግኛት፤ ማስተዋልን ያዛት፤
ቃሌን አትርሳ፤ ከእርሷም ዘወር አትበል።
6ጥበብን አትተዋት፤ እርሷም ከለላ ትሆንሃለች፤
አፍቅራት፤ እርሷም ትጠብቅሃለች።
7ጥበብ ታላቅ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፤
ያለህን ሁሉ#4፥7 ወይም ያገኘኸውን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት።
8ክብርን ስጣት፤ ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤
ዕቀፋት፤ ታከብርሃለች፤
9በራስህ ላይ ሞገሳማ አክሊል ትደፋልሃለች፤”
የክብር ዘውድም ታበረክትልሃለች።
10ልጄ ሆይ፤ አድምጠኝ፤ ቃሌንም ልብ በል፤
የሕይወት ዘመንህም ትበዛለች።
11በጥበብ ጐዳና አስተምርሃለሁ፤
ቀጥተኛውንም መንገድ አሳይሃለሁ።
12ስትሄድ ርምጃህ አይሰናከልም፤
ስትሮጥም አትደናቀፍም።
13ምክርን አጥብቀህ ያዛት፤ አትልቀቃት፤
ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና።
14ወደ ኀጥኣን ጐዳና እግርህን አታንሣ፤
በክፉ ሰዎች መንገድ አትሂድ፤
15ከዚያ አትድረስ፤ አትጓዝበት፤
ሽሸው፤ መንገድህን ይዘህ ሂድ፤
16ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፤
ሰውን ካላሰናከሉ እንቅልፍ በዐይናቸው አይዞርም።
17የክፋት እንጀራ ይበላሉ፤
የዐመፅ ወይን ጠጅ ይጠጣሉ።
18የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣
ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው።
19የክፉዎች መንገድ ግን እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነው፤
ምን እንደሚያሰናክላቸውም አያውቁም።
20ልጄ ሆይ፤ የምነግርህን አስተውል፤
ቃሌንም በጥንቃቄ አድምጥ።
21ከእይታህ አታርቀው፤
በልብህም ጠብቀው፤
22ለሚያገኘው ሕይወት፤
ለመላው የሰው አካልም ጤንነት ነውና።
23ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤
የሕይወት ምንጭ ነውና።
24ጥመትን ከአፍህ አስወግድ፤
ብልሹ ንግግርም ከከንፈሮችህ ይራቅ።
25ዐይኖችህ በቀጥታ ይመልከቱ፤
ትክ ብለህም ፊት ለፊት እይ።
26የእግርህን ጐዳና አስተካክል፤#4፥26 ወይም ተመልከት
የጸናውን መንገድ ብቻ ያዝ።
27ወደ ቀኝ ወደ ግራ አትበል፤
እግርህን ከክፉ ጠብቅ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.