መዝሙር 40

40
መዝሙር 40
40፥13-17 ተጓ ምብ – መዝ 70፥1-5
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፤
እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ።
2ከሚውጥ ጕድጓድ፣
ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤
እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤
አካሄዴንም አጸና።
3ለአምላካችን የሚሆን ውዳሴ፣
አዲስ ዝማሬን በአፌ ላይ አኖረ፤
ብዙዎች ያያሉ፤ ይፈራሉም፤
እግዚአብሔር ይታመናሉ።
4ብፁዕ ነው፤
እግዚአብሔርን መታመኛው ያደረገ፣
ወደ ትዕቢተኞች የማይመለከት፣
የሐሰት አማልክትን#40፥4 ወይም ሐሰትን ወደሚከተሉት ተብሎ መተርጐም ይችላል። ወደሚከተሉት የማያይ፤
5 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤
አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤
ለእኛ ያቀድኸውን፣
ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤
ላውራው ልናገረው ብል፣
ስፍር ቍጥር አይኖረውም።
6መሥዋዕትንና ቍርባንን አልፈለግህም፤
ጆሮዎቼን ግን ከፈትህ፤#40፥6 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን፣ አካልን ግን አዘጋጀህልኝ ይላል።
የሚቃጠል መሥዋዕትን፣
የኀጢአትንም መሥዋዕት አልሻህም።
7እኔም እንዲህ አልሁ፤ “እነሆ፤ መጥቻለሁ፤
ስለ እኔ በመጽሐፍ ተጽፏል፤
8አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤
ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።”
9በታላቅ ጉባኤ ውስጥ ጽድቅን አበሠርሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ እንደምታውቀው፣
ከንፈሮቼን አልገጠምሁም።
10ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤
ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤
ምሕረትህንና እውነትህን፣
ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤
ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤
12ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከብቦኛልና፤
የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤
ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዝቷል፤
ልቤም ከድቶኛል።
13 እግዚአብሔር ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
14ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ
ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤
ጕዳቴንም የሚሹ፣
ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ።
15በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣
በራሳቸው ዕፍረት ይደንግጡ።
16አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣
ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤
ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወድዱ፣
እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ።
17እኔ ግን ችግረኛና ድኻ ነኝ፤
ጌታ ግን ያስብልኛል።
አንተ ረዳቴና ታዳጊዬም ነህና፤
አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ።

Currently Selected:

መዝሙር 40: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ