መዝሙር 50
50
መዝሙር 50
የአሳፍ መዝሙር።
1ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር ተናገረ፤
ከፀሓይ መውጫ እስከ ፀሓይ መግቢያ ድረስ ምድርን ጠራት።
2ፍጹም ውብ ከሆነችው ከጽዮን፣
እግዚአብሔር አበራ።
3አምላካችን ይመጣል፤ ዝምም አይልም፤
የሚባላ እሳት በፊቱ፣
የሚያስፈራ ዐውሎ ነፋስም በዙሪያው አለ።
4በሕዝቡ ይፈርድ ዘንድ፣
በላይ ያለውን ሰማይንና ምድርን እንዲህ ብሎ ይጠራል፤
5“በመሥዋዕት ከእኔ ጋራ ኪዳን የገቡትን፣
ቅዱሳኔን ወደ እኔ ሰብስቧቸው።”
6ሰማያት ጽድቁን ያውጃሉ፤
እግዚአብሔር ራሱ ፈራጅ ነውና። ሴላ
7“ሕዝቤ ሆይ፤ ስማኝ፤ ልንገርህ፤
እስራኤል ሆይ፤ በአንተ ላይ ልመስክር፤
አምላክህ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
8ስለ መሥዋዕትህ አልነቀፍሁህም፤
የሚቃጠል መሥዋዕትህማ ሁልጊዜ በፊቴ ነው።
9እኔ ግን ኰርማህን ከበረት፣
ፍየሎችህንም ከጕረኖ የምፈልግ አይደለሁም፤
10የዱር አራዊት ሁሉ፣
በሺሕ ተራሮች ላይ ያለውም እንስሳ የእኔ ነውና።
11በየተራራው ያለውን ወፍ ሁሉ ዐውቃለሁ፤
በሜዳ የሚገኘው ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ የእኔ ነው።
12ብራብ ለአንተ አልነግርህም፤
ዓለምና በውስጧ ያለውም ሁሉ የእኔ ነውና።
13ለመሆኑ፣ እኔ የኰርማ ሥጋ እበላለሁን?
የፍየልንስ ደም እጠጣለሁን?
14“ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት አቅርብ፤
ለልዑልም ስእለትህን ስጥ።
15በመከራ ጊዜ ወደ እኔ ጩኽ፤
አድንሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ።”
16ክፉውን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፤
“ሕጌን ለማነብነብ፣
ኪዳኔንም በአፍህ ለመናገር ምን መብት አለህ?
17ተግሣጼን ትጠላለህና፤
ቃሌንም ወደ ኋላህ ትጥላለህ።
18ሌባውን ስታይ ዐብረኸው ነጐድህ፤
ዕድል ፈንታህንም ከአመንዝሮች ጋራ አደረግህ።
19አፍህን ለክፋት አዋልህ፤
አንደበትህም ሽንገላን ጐነጐነ።
20ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፤
የእናትህንም ልጅ ስም አጐደፍህ።
21ይህን አድርገህ ዝም አልሁ፤
እንደ አንተ የሆንሁ መሰለህ።
አሁን ግን እገሥጽሃለሁ፣
ፊት ለፊትም እወቅሥሃለሁ።
22“እናንተ እግዚአብሔርን የምትረሱ፤ ይህን ልብ በሉ፤
አለዚያ ብትንትናችሁን አወጣለሁ፤
የሚያድናችሁም የለም።
23የምስጋናን መሥዋዕት የሚሠዋ ያከብረኛል፤
መንገዱንም ቀና ለሚያደርግ#50፥23 ወይም መንገዱን ለሚገነዘብ ተብሎ መተርጐም ይችላል።፣
የእግዚአብሔርን ማዳን አሳየዋለሁ።”
Currently Selected:
መዝሙር 50: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.