የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 66

66
መዝሙር 66
ለመዘምራን አለቃ፤ ማሕሌት፤ መዝሙር።
1ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል ይበል!
2ለስሙ ክብር ዘምሩ፤
ውዳሴውንም አድምቁ።
3እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፤ “ሥራህ እንዴት ግሩም ነው!
ጠላቶችህ ከኀይልህ ታላቅነት የተነሣ፣
በፊትህ ይርዳሉ።
4ምድር ሁሉ ይሰግድልሃል፤
በዝማሬ ያመሰግኑሃል፤
ለስምህም ይዘምራሉ።” ሴላ
5ኑና፣ እግዚአብሔር ያደረገውን እዩ፤
በሰዎች መካከል ሥራው አስፈሪ ነው!
6ባሕሩን የብስ አደረገው፤
ወንዙን በእግር ተሻገሩ፤
ኑ፣ በርሱ ደስ ይበለን።
7በኀይሉ ለዘላለም ይገዛል፤
ዐይኖቹ ሕዝቦችን ይመለከታሉ፤
እንግዲህ ዐመፀኞች ቀና ቀና አይበሉ። ሴላ
8ሕዝቦች ሆይ፤ አምላካችንን ባርኩ፤
የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ።
9እኛን በሕይወት የሚያኖረን፣
እግራችንንም ከመንሸራተት የሚጠብቅ እርሱ ነው።
10አምላክ ሆይ፤ አንተ ፈተንኸን፤
እንደ ብርም አነጠርኸን።
11ወደ ወጥመድ አገባኸን፤
በጀርባችንም ሸክም ጫንህብን።
12ሰዎች በራሳችን ላይ እንዲፈነጩ አደረግህ፤
በእሳትና በውሃ መካከል ዐለፍን፤
የኋላ ኋላ ግን ወደ በረከት አመጣኸን።
13የሚቃጠል መሥዋዕት ይዤ ወደ መቅደስህ እገባለሁ፤
ስእለቴንም ለአንተ እፈጽማለሁ፤
14በመከራ ጊዜ ከአፌ የወጣ፣
በከንፈሬም የተናገርሁት ስእለት ነው።
15ፍሪዳዎችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ፣
አውራ በጎችንም የሚጤስ ቍርባን አድርጌ አቀርብልሃለሁ፤
ኰርማዎችንና ፍየሎችንም እሠዋልሃለሁ። ሴላ
16እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ፤ ኑና ስሙ፤
ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ።
17በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፤
በአንደበቴም አመሰገንሁት።
18ኀጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ፣
ጌታ ባልሰማኝ ነበር።
19አሁን ግን እግዚአብሔር በርግጥ ሰምቶኛል፤
ጸሎቴንም አድምጧል።
20ጸሎቴን ያልናቀ፣
ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ፣
እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው።

Currently Selected:

መዝሙር 66: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ