መዝሙር 92
92
መዝሙር 92
በሰንበት ቀን የሚዘመር መዝሙር፤ ማሕሌት።
1 እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፤
ልዑል ሆይ፤ ለስምህ መዘመር ጥሩ ነው፤
2ምሕረትህን በማለዳ፣
ታማኝነትህንም በሌሊት ማወጅ መልካም ነው፤
3ዐሥር አውታር ባለው በገና፣
በመሰንቆም ቅኝት ታጅቦ ማወጅ ጥሩ ነው።
4 እግዚአብሔር ሆይ፤ በሥራህ ስለ ተደሰትሁ፣
ስለ እጅህ ሥራ በደስታ እዘምራለሁ።
5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ታላቅ ነው!
ሐሳብህስ ምን ያህል ጥልቅ ነው!
6ደነዝ ሰው ይህን አያውቅም፤
ሞኝም አያስተውለውም።
7ክፉዎች እንደ ሣር ቢበቅሉ፣
ክፉ አድራጊዎች ቢለመልሙ፣
ለዘላለሙ ይጠፋሉ።
8 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ።
9ጠላቶችህ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፤
ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይበተናሉ።
10የእኔን ቀንድ ግን እንደ አውራሪስ ቀንድ#92፥10 ጥንካሬን የሚያመለክት ነው። ከፍ ከፍ አደረግኸው፤
በለጋ ዘይትም አረሰረስኸኝ።
11ዐይኖቼ የባላንጦቼን ውድቀት አዩ፤
ጆሮዎቼም የክፉ ጠላቶቼን ድቀት ሰሙ።
12ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ፤
እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይንዠረገጋሉ።
13በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤
በአምላካችንም አደባባይ ይንሰራፋሉ።
14ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤
እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ።
15“እግዚአብሔር ትክክለኛ ነው፤
እርሱ ዐለቴ ነው፤ በርሱ ዘንድ እንከን የለም” ይላሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.