ራእይ 12
12
ሴቲቱና ዘንዶው
1ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሓይን የለበሰች፣ ጨረቃን ከእግሮቿ በታች የረገጠችና በራሷም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉት አክሊል የደፋች አንዲት ሴት ታየች። 2እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድ ስትል ምጥ ይዟት ተጨንቃ ጮኸች። 3ከዚያም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት አክሊል የደፋ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ። 4ጅራቱ የከዋክብትን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ እርሷም በወለደች ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ዘንዶው ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ። 5ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።#12፥5 መዝ 2፥9 6ሴቲቱም አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ክብካቤ እንዲደረግላት እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላት ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች።
7በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋራ ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤ 8ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ። 9ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከርሱ ጋራ ተጣሉ።
10ከዚህ በኋላ ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
“አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልና
መንግሥት፣
የርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቷል።
ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከስሳቸው
የነበረው፣
የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሏልና።
11እነርሱም በበጉ ደም፣
በምስክርነታቸውም ቃል፣
ድል ነሡት፤
እስከ ሞት ድረስ እንኳ፣
ለነፍሳቸው አልሳሱም።
12ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣
በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣
ደስ ይበላችሁ፤
ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ
እንደ ቀረው ስላወቀ፣
በታላቅ ቍጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።”
13ዘንዶው ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ፣ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። 14ሴቲቱም በበረሓ ወደ ተዘጋጀላት ስፍራ በርራ መሄድ እንድትችል ሁለት የታላቁ ንስር ክንፎች ተሰጣት፤ ይህም የሆነው በዚያ ከእባቡ ፊት ርቃ ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ በክብካቤ እንድትኖር ነው። 15እባቡም ሴቲቱ በጐርፍ እንድትወሰድ፣ እንደ ወንዝ ያለ ውሃ ከአፉ ተፋ። 16ምድር ግን ሴቲቱን ረዳቻት፤ አፏንም ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠች። 17ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጣ፤ ከቀሩት ልጆቿም ጋራ ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው።
Currently Selected:
ራእይ 12: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.