አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15
15
ሳኦል በዐማሌቃውያን ላይ ያደረገው ጦርነት
1ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቀብቼ እንዳነግሥህ እግዚአብሔር የላከኝ እኔ ነኝ፤ አሁንም ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር የሚለውን ስማ፤ #1ሳሙ. 10፥1። 2እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ አማሌቃውያን በመንገድ ላይ እየተቃወሙ አስቸግረዋቸው ስለ ነበረ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ለመቅጣት ወስኖአል። #ዘፀ. 17፥8-14፤ ዘዳ. 25፥17-19። 3ሄደህ በዐማሌቃውያን ላይ አደጋ በመጣል ያላቸውን ሁሉ ደምስስ፤ ከእነርሱ ምንም ነገር አታስቀር፤ ወንዶችን፥ ሴቶችን፥ ልጆችንና ሕፃናትን፥ ከብቶችን፥ በጎችን፥ ግመሎችንና አህዮችን ሁሉ ግደል።”
4ሳኦልም ሠራዊቱን በአንድነት ጠርቶ ጤሌም በሚባል ስፍራ ቈጠራቸው፤ የወታደሮቹም ብዛት ከእስራኤል ሁለት መቶ ሺህ ከይሁዳ ዐሥር ሺህ ሆነው ተገኙ፤ 5ከዚያም እርሱና ሠራዊቱ ወደ ዐማሌቃውያን ከተማ ሄደው በአንድ ደረቅ ጅረት ውስጥ ደፈጣ አደረጉ፤ 6“እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ ቸርነት ስላደረጋችሁላቸው እናንተን ከአማሌቃውያን ጋር እንዳላጠፋ ከዐማሌቃውያን ተለይታችሁ ሂዱ” ብሎ ሳኦል ለቄናውያን ነገራቸው። እነርሱም ከዐማሌቃውያን ተለይተው ሄዱ።
7ሳኦል ከሐዊላ ጀምሮ በግብጽ ምሥራቅ እስከምትገኘው እስከ ሹር በሚያደርሰው መንገድ ሁሉ ዐማሌቃውያንን ድል አደረገ። 8የዐማሌቅ ንጉሥ የነበረውን አጋግን በሕይወት ማርኮ፥ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ፈጀ፤ 9ነገር ግን ሳኦልና ሠራዊቱ የአጋግን ሕይወት አተረፉ፤ እንዲሁም ምርጥ ምርጥ የሆኑትን በጎችና የቀንድ ከብቶች፥ የሰቡ ሰንጋዎችንና ጠቦቶችን ከዚህም ጋር መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አላጠፉም፤ እነርሱም ያጠፉት የማይረባውንና የማይጠቅመውን ነገር ብቻ ነበር።
ሳኦል በንጉሥነት መቀጠል እንደማይችል መነገሩ
10እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ 11“ሳኦል እኔን ትቶአል፤ ትእዛዜንም ስላልጠበቀ እርሱን በማንገሤ ተጸጸትሁ፤” ሳሙኤልም በዚህ ነገር ተቈጥቶ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ ማለደ፤ 12በማግስቱም ማለዳ በመነሣት ሳኦልን ፈልጎ ለማግኘት ሄደ፤ ሳኦል ለራሱ ሐውልት ወዳቆመባት ወደ ቀርሜሎስ ከተማ ከደረሰ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልጌላ መሄዱን ሰማ፤ 13ሳሙኤል ወደ ሳኦል ሄደ፤ ሳኦልም “ሳሙኤል ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክህ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው።
14ሳሙኤልም “ታዲያ ይህ የምሰማው የቀንድ ከብትና የበግ መንጋ ድምፅ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
15ሳኦልም “እነርሱ ወታደሮቼ ከዐማሌቃውያን የማረኩአቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጥ የሆኑትን የቀንድ ከብቶችና በጎች ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ አምጥተዋል፤ የቀሩትን ግን በሙሉ ደምስሰናል” ሲል መለሰለት።
16ሳሙኤልም “ተወው በቃ፤ እግዚአብሔር ትናንትና ማታ የገለጠልኝን እነግርሃለሁ” አለው።
ሳኦልም “እሺ ንገረኝ” አለ።
17ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንተ ስለ ራስህ የነበረህ ግምት አነስተኛ ቢሆንም የእስራኤል ነገዶች መሪ አልሆንክምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል፤ 18ኃጢአተኞች የሆኑትን እነዚያን አማሌቃውያንን እንድትደመስስ ልኮሃል፤ እስኪጠፉም ድረስ እነርሱን ግደል ብሎ ነግሮሃል። 19ታዲያ ስለምን ትእዛዙን አልፈጸምክም? ለምርኮስ በመሳሳትና በመስገብገብ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ነገር ስለምን አደረግህ?”
20ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ፤ ባዘዘኝም መሠረት ዘምቻለሁ፤ ንጉሥ አጋግን ብቻ ማርኬ ሳመጣ ሌሎችን ዐማሌቃውያን ሁሉ ገድያለሁ፤ 21ነገር ግን ወታደሮቼ የማረኩአቸውን ምርጥ ምርጥ የሆኑ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን አልገደሉአቸውም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ አምጥተዋቸዋል።”
22ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የሚወደው የቱን ይመስልሃል? መታዘዝን ወይስ ቊርባንና መሥዋዕት ማቅረብን? ለእርሱ መታዘዝ ምርጥ የበግ መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ 23በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ እንደ ሟርተኛነት፥ የትዕቢት እልኸኛነትም ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት እንደ መሥራት ይቈጠራል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ተውክ በንጉሥነትህ እንዳትቀጥል እርሱም አንተን ትቶሃል።”
24ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አዎ፤ እኔ ኃጢአት ሠርቼአለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና አንተ የሰጠኸኝን መመሪያ አልጠበቅሁም፤ ወታደሮቼን በመፍራት እነርሱ የፈለጉትን ሁሉ አደረግሁ፤ 25አሁን ግን እለምንሃለሁ በደሌን ይቅር በለኝ፤ በዚያ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔም ጋር ወደ ጌልጌላ ተመለሰ።”
26ሳሙኤልም “እኔ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ትተሃል፤ አንተም የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ እንዳትቀጥል እርሱ ትቶሃል” ሲል መለሰለት።
27ከዚያም በኋላ ሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን መለሰ፤ ሳኦል ግን ሳሙኤል እንዳይሄድበት የካባውን ጠርዝ ሲይዝ ተቀደደ፤ 28ሳሙኤልም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ዛሬ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ቀዶ ከእጅህ በመውሰድ ለተሻለ ለሌላ ሰው ሰጥቶታል፤ #1ሳሙ. 28፥17፤ 1ነገ. 11፥30-31። 29የእስራኤል ክብር የሆነ እግዚአብሔር አያብልም፤ ሐሳቡንም አይለውጥም፤ እርሱ እንደ ሰው ስላልሆነ ሐሳቡን አይለውጥም።”
30ሳኦልም “በእርግጥ በደል ሠርቼአለሁ፤ ይሁን እንጂ ሌላው ቢቀር በሕዝቤ መሪዎችና በእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ፊት አክብረኝ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር አብረህ ሂድ” ሲል ለመነው። 31ስለዚህም ሳሙኤል አብሮት ወደ ጌልጌላ ሄደ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።
32ሳሙኤልም “ንጉሥ አጋግን ወደዚህ አምጣልኝ!” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ አጋግም በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ፤ በልቡም “ሞት እንዴት መራራ ናት!” እያለ ያስብ ነበር፤ 33በዚህም ጊዜ ሳሙኤል “የአንተ ሰይፍ ብዙዎች እናቶችን ልጅ አልባ እንዳደረገቻቸው፥ የአንተም እናት ልጅ አልባ ሆና ትቀራለች” አለው። ከዚህም በኋላ በጌልገላ በሚገኘው በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት አጋግን ቈራርጦ ጣለው።
34ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ወደ ራማ ሄደ፤ ንጉሥ ሳኦልም ወደ ጊብዓ ተመለሰ። 35ከዚያን ሰዓት ጀምሮ ሳሙኤል በነበረበት ጊዜ ሁሉ ንጉሥ ሳኦልን በዐይኑ አላየውም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጽቶ ስለ ነበር፥ ለእርሱ በማዘን ያለቅስለት ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997